ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የጨጓራ ሕመም አስጊ ምልክቶች

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በኢትዮጵያ እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል የጨጓራ ሕመም ተጠቂ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ለሕመሙ መከሰት ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው “ፈንክሽናል ዲስፔፕሲያ” የተባለውና ግልጽ የሆነ የሰውነት አካል ጉዳት ሳይኖር የሚከሰተው የሕመም ዓይነት ነው።

ሕመሙ በአብዛኛው በላይኛው የሆድ ክፍል ላይ የማቃጠል፣ የመሙላት እና ምቾት የማጣት ስሜት እንደሚፈጥር በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ሐሴት ለገሰ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።

የጨጓራ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን፣ የቁስለት ሕመም፣ የሐሞት ከረጢት ችግር እንዲሁም ያላግባብ የሚወሰዱ የሕመም ማስታገሻና የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶች ለችግሩ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው።

ዶ/ር ሐሴት በተለይም ሕመምተኞች አስጊ ምልክቶችን ለይተው በማወቅ ፈጣን የሕክምና ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከእነዚህም መካከል ያልተፈለገ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ ተደጋጋሚ ትውከት፣ ምግብ ለመዋጥ መቸገር፣ ደም ማስመለስ እና የሰገራ ቀለም ወደ ጥቁርነት መቀየር የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ያለምክንያት የሚከሰት የደም ማነስና በሆድ አካባቢ የሚታይ እብጠትም አስቸኳይ ትኩረት የሚሹ ምልክቶች ናቸው።

በተለይም እድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑና አዲስ የጨጓራ ሕመም የጀመራቸው ወይም በቤተሰባቸው ውስጥ የጨጓራ ካንሰር ታሪክ ያለባቸው ሰዎች ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

የምርመራ ሂደቱን በተመለከተ ታካሚዎች እንደ ሁኔታው የባክቴሪያ ወይም የውስጥ አካል (ኢንዶስኮፒ) ምርመራ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ዶ/ር ሐሴት የገለጹ ሲሆን፣ ሕክምናውም እንደ መንስኤው ዓይነት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ከባክቴሪያ ውጭ ለሚከሰቱ የጨጓራ ሕመሞች ደግሞ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም ቅባታማ ምግቦችን መቀነስ፣ አነስተኛ መጠን ያለው ምግብ ደጋግሞ መመገብ፣ አልኮልን ማስወገድ እና ጭንቀትን መቆጣጠር ለውጥ እንደሚያመጣ ዶ/ር ሐሴት ገልጸው፣ ሕመምተኞች ምልክቶቹ ሳይበረቱ ቀድመው ምርመራ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ViaAMN


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: