የአይ.ኤም.ኤፍ እና የኢትዮጵያ መንግሥት 5ኛውን የኢኮኖሚ ግምገማ ጀመሩ፤ የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ተፅዕኖ የውይይቱ ትኩረት ሆኗል
#Ethiopia | በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአምስተኛው የተራዘመ ብድር አቅርቦት ፕሮግራም ክለሳ ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል።
የዚህ ውይይት ዋነኛ ትኩረት በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ የፖሊሲ እርምጃዎችን መቀየስ ነው።
ወይዘሮ ጆርጂየቫ ናይሮቢ ለሚካሄደው የ”Africa Forward” ጉባኤ ሲጓዙ አዲስ አበባ ላይ በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም የውጭ ተፅዕኖዎች የሀገሪቱን ጥንካሬ እየፈተኑ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ቢኖርም፣ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ባሳየችው ጠንካራ እድገት፣ የወጪ ንግድ አፈጻጸም እና ከመንግስት ገቢ አሰባሰብ አንጻር ለገጠማት ድንገተኛ ጫና ዝግጁ ሆና መገኘቷን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነት በተለይም የሆርሙዝ የባህር በር መዘጋት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ነዳጅን ሙሉ በሙሉ ከውጭ የምታስገባ በመሆኗ ለዋጋ ንረት ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል።
ከዚህ በተጨማሪ የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር በግብርናው ዘርፍ ላይ ጫና እየፈጠረ ሲሆን፣ ከወርቅ ውጭ ካለው የወጪ ንግድ 19 በመቶው እና ከሃዋላ ገቢ 35 በመቶው ከመካከለኛው ምስራቅና ከባህረ ሰላጤው ሀገራት የሚገኝ በመሆኑ አካባቢው በከፍተኛ ክትትል ስር እንዲውል አድርጓል።
ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ አምስተኛ ክለሳ ወቅት ሀብትን በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ማዋል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አሳስበው፣ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መንግስት ጥብቅ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲን መከተል እንዳለበት መክረዋል።
በተለይም እንደ ነዳጅ ድጎማ ወይም አጠቃላይ የቀረጥ ቅነሳ ያሉ ኢላማቸውን ያልጠበቁ እርምጃዎች በከፍተኛ ዋጋ ምክንያት የሚመጣውን ስቃይ ከማራዘም ውጭ ፋይዳ እንደሌላቸው በመጥቀስ፤ መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት እና በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘላቂነት መካከል ጥንቃቄ የተሞላበት ሚዛን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
በአይኤምኤፍ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው አጋርነት ተጠናክሮ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ከተጀመረ አንስቶ ድርጅቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ መልቀቁና ባለፈው ጥር ወር አራተኛው ክለሳ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በጋራ ማዕቀፍ ስር እያከናወነች ያለው የዕዳ ሽግሽግ ሂደት ከሌሎች ሀገራት በበለጠ ፍጥነት እየተጓዘ መሆኑን ያደነቁት ጆርጂየቫ፣ ይህም ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ትልቅ የቁርጠኝነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን በቴክኒክ ባለሙያዎች ደረጃ የቀጠለው አምስተኛው ክለሳ ዋና ዓላማው የሀገር በቀል ማሻሻያው በክልላዊ አለመረጋጋት ሳይደናቀፍ ይልቁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻል ነው።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
#ቅዳሜገበያ#etbusinessview
#Ethiopia
Source: GetuTemesgen









No comments yet.