#Fastmereja:በአዲስ አበባ ከተማ ለሁለት አስርት ዓመታት የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የአራዳ ሕክምና ማዕከል (አራዳ ጊዮርጊስ ጠቅላላ ሆስፒታል)፣ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በዛሬው ዕለት በተለያዩ ኩነቶች አክብሯል።
ማዕከሉ በምስረታ በዓሉ ዕለት በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት እጥረት ይቀርፋል የተባለለትን የጆሮ፣ አፍንጫ እና ጉሮሮ (ENT) ከፍተኛ ስፔሻላይዝድ ክሊኒክ በዛሬዉ እለት በይፋ መርቆ አገልግሎት አስጀምሯል።
የማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ነጋ ገብረሚካኤል በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በ1998 ዓ.ም በትንሽ ክሊኒክ ደረጃ ጉዞውን የጀመረ ቢሆንም፣ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
ተቋሙ ከሕክምናው ጎን ለጎን በጤና ባለሙያዎች ስልጠና ላይ በመሰማራትም እስካሁን ከ3,500 በላይ ነርሶችንና የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ለሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ማበርከቱ ተገልጿል።
ዛሬ በይፋ የተመረቀው ከፍተኛ የጆሮ፣ አፍንጫ እና ጉሮሮ (ENT) ስፔሻላይዝድ ክሊኒክ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይህን ልዩ አገልግሎት ከሚሰጡ ጥቂት (አምስት) ተቋማት አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ክሊኒኩ በዘርፉ አዲስ የሆነውን የሌዘር ማሽን (Laser Machine) በመጠቀም ደም መፍሰስን የሚቀንስ እና ስቃይ የሌለው ቀዶ ሕክምና መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በተጨማሪም አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት የመስማት ችሎታ ምርመራ (Audiology) እና የስፒች ቴራፒ አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል።
ማዕከሉ የ20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት በርካታ የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በመንግሥት ሆስፒታሎች ረጅም የቀጠሮ ዝርዝር ውስጥ የነበሩ 20 ሕፃናትን በነፃ ቀዶ ጥገና ማድረግ፣ ለአረጋውያን ዘመናዊ የጆሮ ምርመራ (Endoscopy and Audiometry) በነፃ መስጠት፣ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ነፃ የ ENT ምርመራ ማከናወን ይገኙበታል።
በተጨማሪም ማዕከሉ በቀጣይ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል (Digital Health) የመቀየር ራዕይ የሰነቀ ሲሆን ለኩላሊት እጥበት (Dialysis) እና ለካንሰር ሕክምና የሚውል ቦታ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንና አገልግሎቶቹን በቅርቡ ለመጀመር ማቀዳቸውን በእለቱ ተገልጿል።
በመጨረሻም ላለፉት 20 ዓመታት በማዕከሉ ነፃ ሕክምና ሲደረግላቸው የቆዩ ታካሚዎች ምስጋናቸዉን ያቀረቡ ሲሆን፣ማዕከሉ ከሕክምና አገልግሎቱ ጎን ለጎን ከዩኤስ ኤይድ (USAID) ጋር በመተባበር በኤች አይ ቪ (HIV) ምርመራና በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በስፋት ሲሳተፍ መቆየቱ ተገልጿል።



Source: FastMereja








No comments yet.