> ታሪከኛዋ አትሌት ከጋና

- Advertisement -
Sidebar AD

<< ለሀገሬ ታሪክ እንደምሰራ ታውቋቸው ይሆናል>‼️

አጃኢብ የሚያስብል ድል ከወደ ጋና፥ ከዋና ከተማዋ አክራ፥ ከሌገን ስፖርትስ ስታዲየም፥ በ24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ትናንት ተመዝግቧል

ኢትዮጵያ ምሽቱን በሜዳሊያ ተንበሽብሻለች፤ 3 ወርቅና 2 ነሀስ በጥቅሉ አምስት ሜዳሊያዎችን ትናንት ብቻ አግኝታለች፥ አጃኢብ ነው!

በ800 ሜትር ሴቶች ምስጋና ሀይሉ እንዲሁም በወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ገመቹ ጎዳና የወርቅ ሜዳሊያ አጠለቁ፤ በፀሎት አለማየሁ በከፍታ ዝላይና ሳሙኤል ፍሬው በ3ሺህ መሰናክል ነሀስ ሜዳሊያ አመጡ

ሌላኛው አጃኢብ የሚያስብለው ውጤት በ400 ሜትር ሴቶች የተመዘገበው ልዩ ድል ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ርቀት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች፤ የመጀመሪያ ማጣሪያና የግማሽ ፍፃሜ ውድድሩን በብቃት የተወጣችው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አዲስ ታሪክ ፅፋለች፥ አጃኢብ ነው!

ስሟ ደግሞ አጃይባ

ርቀቱን 51.54 ገብታ አሸንፋለች፤ የቦትስዋናና የጋና አትሌቶችን አስከትላ የወርቅ ሜዳሊያዋን ካጠለቀች በኋላ፥ ሰንደቅ አላማውን ከፍ አድርጋ ካሰቀለች በኋላ፥ ብሄራዊ መዝሙሩን ካዘመረች በኋላ በዶ/ር ትዕዛዙ ሞሴ ትብብር ለአጭር ቆይታ በስልክ አወራኋት፤ እንኳን ደስ አለሽ አልኩና የመጀመሪያ ጥያቄዬ ይህ ሆነ፦

➡️ እንደው ቤተሰቦችሽ ምን ታይቷቸው ነው አጃይባ ያሉሽ?

📞 እኔንጃ ምናልባት በሩጫው ለሃገሬ ታሪክ እንደምሰራ ታውቋቸው ይሆን? እስኪ እጠይቃቸዋለሁ(ሳቅ)

➡️ አጃይባን በአጭሩ እንተዋወቃት?

📞 እሺ አጃይባ አልዬ እባላለሁ፤ አባቴ አልዬ አህመድ፥ እናቴ መሪማ የሱፍ ይባላሉ፤ ለቤቱ ስድስተኛ ልጅ ነኝ

➡️ ቤታችሁ የአትሌቶች መፍለቂያ ነው ይባላል? እውነት ነው?

📞 አዎ እህቴ በይቱላ አልዬ የ100ና 200 ሜትር ሯጭ ነች፤ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሆናለች፤ ኢትዮጵያን ወክላም ተሳትፋለች፤ አሁንም ከጉዳት አገግማ እየሮጠች ነው፤ ታናሽ እህቴም የ100 ሜትር ሯጭ ነች፤ ሁላችንም እንደ ዲባባ ቤተሰብ ለሀገራችን ታሪክ የመስራት ህልም አለን

➡️ የትውልድ ቦታ?

📞 ስልጤ ዞን፥ ምስራቅ ስልጢ ወረዳ፥ገርቤበር ከተማ

➡️ እድሜሽ?

📞 ባለፈው ወር 19 አመት ሞላኝ

➡️ ክለብሽ?

📞 ሲዳማ ቡና

➡️ ለዚህ የአፍሪካ ውድድር ያደረግሽው ዝግጅት ምን ይመስል ነበር?

📞 ሀገር ቤት እያለሁ በደንብ ተዘጋጅቼ ነበር፤ ትንሽ ፈተናም ነበረው፤ እዚህ በመጀመሪያው ማጣሪያና በግማሽ ፍፃሜው ባሳየሁት አቋም እንደማሸንፍ ታውቆኝ ነበር፤ የእህቴ በይቱላ ምክርም ጠቅሞኛል

➡️ ምን አለችሽ?

📞 ጥሩ አቅም አለሽ፥ በራስ መተማመንሽን ብቻ አሳድጊ ታሳኪዋለሽ ብላኝ ነበር፤ ይኸው ተሳካ፤ አልሃምዱሊላህ!

➡️ በሴቶች በታሪክ በ400 ሜትር ወርቅ ስናገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ ምን ስሜት ፈጠረብሽ? ቀጣይ እቅድሽስ?

📞 ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ነው የምትታወቀው፤ በአጭር ርቀትም ከተሰራበት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው፤ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በአጭር ርቀት ብዙ አቅም ያላቸው አትሌቶች ይኖራሉ፤ እኔም የወጣሁት ከስልጤ ነው፤ የመጀመሪያዋ አሸናፊ በመሆኔም ተደስቻለሁ፤ ደጋግሜ ማሸነፍም እፈልጋለሁ፤ በአለም ሻምፒዮናና በኦሊምፒክ ሃገሬን የማስጠራት ህልም አለኝ፤ አላህ ይርዳኝ

➡️ በዚህ ሻምፒዮና በሌላ ርቀት ትወዳደሪያለሽ?

📞 አዎ በ200 ሜትር እሳተፋለሁ

➡️ የዛሬው ድል መታሰቢያነቱ ለማን ይሁንልሽ?

📞 ለእናቴ መሪማ የሱፍና ለጓደኛዬ ለአትሌት ትዕግስት ይሁንልኝ

➡️ የመጨረሻ መልዕክት ካለሽ

📞 እንኳን ደስ አላችሁ፥ እንኳን ደስ አለን!

➡️ እንደው ይህንን በስልጢኛ በይልኝና እንለያይ

📞 ሀበይ ተስ ባለሙ፥ ሀበይ ተስ ባለነ!

(ታምሩ ዓለሙ)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: