የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ ከኅብረተሰቡ የተገኘን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ባከናወኑት ኦፕሬሽን 405.4 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ክትትል 353.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የገቢ እንዲሁም 51.8 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተያዙ ሲሆን በጅግጅጋ፣ በአዋሽ፣ በሞያሌ እና በሌሎችም የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ቅርንጫፎች በተከናወነ የተጠናከረ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል፤ አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግብርና ምርቶች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ መድኃኒቶች፣ ማዕድናት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳትና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ያጋራው መረጃ ያመላክታል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጸጥታ አካላትና በጉምሩክ ኮሚሽን ባለሙያዎች የተቀናጀ ጥረት በፍተሻ፣ በጥቆማና በበረራ ኦፕሬሽኖች የተያዙ ሲሆን በሕገ-ወጥ ድርጊቱ ላይ የተሳተፉ 10 ተጠርጣሪዎችና ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሰባት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
የኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልት በየጊዜው ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ላይ የሚያሳድረውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመከላከል ኅብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
Ethiopian Federal Police













No comments yet.