የግል ንግድ /sole proprietorship/ እና ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትርጉም፣ልዩነት ጥቅምና

- Advertisement -
Sidebar AD

የግል ንግድ /sole proprietorship/ እና ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትርጉም፣ልዩነት ጥቅምና ስጋት
ከኢትዮጵያ ንግድ ህግ ማእቀፍ

ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው

መግቢያ
#Ethiopia | ለዚህ ጹሁፍ መነሻ የሆነኝ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና የግል ንግድ /sole proprietorship/ ያሉት ባህርያት ፥ የሚለያዩበት መሠረታዊ ነጥብ ፥ የሁለቱም ጥቅም እና የንግድ እንቅስቃሴ ከመደምደሚያ የህግ ምክር ጋር አጠቃለን ለህግ ግንዛቤ ይሆን ዘንድ ለእናንተ አቅርበናል።

1. የግል ንግድ ድርጅት/Sole proprietorship/ የህግ ትርጉም
የግል ንግድ ድርጅት (Sole Proprietorship) ማለት በአንድ ግለሰብ ብቻ የሚመሰረት፣ የሚንቀሳቀስ እና በባለቤትነት የሚተዳደር የንግድ አይነት ነው። ይህ የንግድ መዋቅር በአንድ ሰው የሚመራና ከባለቤቱ የተለየ የህግ ሰውነት የሌለው ንግድ ነው።የንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 አንቀጽ 5 ፥38 እና ተከታዮችን በመረዳት መገንዘብ የሚቻል ነው።

2. ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ትርጓሜ
ባለ አንድ አባል ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማለት አንድ ሰው በግሉ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት የተቋቋመ የንግድ ማኅበር ነው።ማኅበሩ ከአባሉ የተለየና የተነጠለ የራሱ የሕግ ሰውነት አለው።አባሉ የራሱን መዋጮ ሙሉ በሙሉ እስከ ከፈለ ድረስ ማኅበሩ ላይ ለሚፈለገው ዕዳ በግሉ እንደማይጠየቅ በንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/13 አንቀጽ 534 ላይ ተደንግጓል።
3. የግል ንግድ ድርጅትና ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መካከል ያለው ልዩነት

3.1 በግል ንግድ/Sole proprietorship/ ያለውን እንመልከት
በግል የንግድ ስራ ሲከናወን በግል የሚሰራው ሰው ራሱ ለሚመጣው ጥቅም ራሱ ተጠቃሚ ሲሆን ለሚከሰተውም እዳ ደግሞ ከድርጅቱ ጋር በተናጠልም ሆነ በአንድነት ተጠያቂ ይሆናል። ኃላፊነቱ ያልተወሰነ ነው። ነጋዴው ከድርጅቱ የሚለይበት አይደለም። ነጋዴው ከሞተ በመሰረቱ የግል ንግዱ ይቆማል። ወራሾች ግን በራሳቸው ስም የመቀጠል መብት አላቸው።

ቢቀጥሉም በቀድሞ በንግዱ ስም ሳይሆን በራሳቸው ነው። ወራሽ ከሌለው ደግሞ እስከ መጨረሻው ድርጅቱ ይሞታል ወይም ይጠፋል። ወራሾች ግን መቀጠል ከፈለጉም ሆነ ንግዱ በራሳቸው እንዲቀጥል ካልፈለጉ የንግድ ስሙን ከንግድ መዝገብ ማሰረዝ አለባቸው። ግብር አከፋፈል በተመለከተ ከትርፉ ላይ አንዴ ብቻ የሚከፈል ነው። አባሉም ድርጅቱም አንድ ነው። የአባላት ትርፍ ክፍፍል/dividend/ የሚባል የለም። ይህ የንግድ ድርጅቱ ከነጋዴው የተለየ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው ነው።

3.2 ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር
ይህ ማህበሩ ከአባሉ የተለየ ህጋዊ ሰውነት ያለው በራሱ ህጋዊ ጉዳይ ማስኬድ የሚችል ነው። አባሉ አንድ ሰው ሲሆን ኃላፊነቱ የተወሰነ ነው። ማህበሩ ባለው እዳ ኃላፊነት አባሉ አይጠየቅም። ማህበሩ እራሱ የሚጠየቅበት ነው። አባሉ ቢሞት ፣ ቢወጣ ማህበሩ ራሱን ችሎ ይቀጥላል። ባለሀብቶች ይህንን አንድ አባል ሆነው ኃላፊነቱ የተወሰነ ስለሆነ ይመርጡታል። ግብር አከፋፈል ከማህበሩ ትርፍ ከተከፈለ በኋላ አባሉ ካገኘው ትርፍ በድጋሜ ግብር ይከፈላል። አባሉ በአንድነት እና በነጠላ ሊጠየቅ የሚችለው በተለየ ሁኔታ ማህበሩን ለጉዳት የሚዳርግ ጥፋት ከፈጸመ በንግድ ህጉ አንቀጽ 543 መሠረት ተጠያቂ ይሆናል እንጂ በመሠረቱ አይጠየቅም።

4. ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጥቅምና ስጋት

በአዲሱ ንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/13 አንቀጽ 534 እንደተቀመጠው ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የህግ እውቅና የተሰጠው ሲሆን ይህ ለብቻቸው ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ማህበር ለመስራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዲሰሩ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ ተሞክሮ በመውስድ የወጣ የህግ ድንጋጌ ነው። በዚህ መሰረት በግል ንግድ ድርጅት ይልቅ አንድ አባል ሆኖ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሥራት ለሚፈልግ ነጋዴ ይህን አማራጭ መምጣቱ ለሀገራችን አማራጭ የንግድ እንቅስቃሴ ስረአት ከፍተኛ ሚና ያለው ነው።

ምክንያቱም ብቻውን አባል ሆኖ በግል ድርጅት ለሚመጣው እዳ ኃላፊነት ባለቤቱ በነጠላ እና በአንድነት ከመጠየቅ ይልቅ ድርጅቱ ብቻ በኃላፊነቱ እንዲጠየቅ አባሉ በማህበሩ እዳ እንዳይጠየቅ እንዲሁም ደግሞ ባለሀብቱ ብቻውን ለመስራት ከፈለገ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን መመሥረት አዋጭ ነው።

የማህበሩ እዳም ወደ አባሉ የማይመጣ ማህበሩ በራሱ የሚጠየቅ ነው። አባሉ ቢወጣ፣ቢሞት ማህበሩ ዘላቂ በመሆኑ ለንግድ እንቅስቃሴ ዋስትና ወሳኝ ሚና አለው። ለሶስተኛ ወገኖች ባለገንዘቦች ግን አንድ አባል ሆኖ ኃላፊነቱ የተገደበ መሆኑ እዳን ከመክፈል አንጻር የሚተማመኑበት አይሆንም። ግብር አከፋፈል ላይ ከማህበሩም ከአባል ትርፉም አንድ ሆኖ ሳለ ሁለቴ መክፈሉ ባለሀብቱን በዚህ ንግድ ማህበር እንዳይሳተፍ የሚገፋው ነው። አንድ አንድ ሀገሮች አንድ ግብር ክፍያ በማድረግ የሚያበረታቱ ሲሆን አሜሪካ ለዚህ ተጠቃሽ ናት።

5. የግል ንግድ ጥቅምና ስጋት

የግል ንግድ/sole proprietorship/ ለሚሰራ ሰው ለ3ኛ ወገኖች ባለገንዘቦች ይህ ተመራጭ ሲሆን ግብር አከፋፈል ላይም አንዴ በንግድ ድርጅቱ ብቻ የሚከፍልበት ነው። አባል ባለ አክስዮን ስለሌለበትም ትርፍ ድርሻ ከፍፍል የለም። እንደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሁለት ጊዜ ግብር አይከፍልም። ያለው ስጋት እዳ ጠያቂዎች ከድርጅቱ አልፈው በግል ሀብቱ ጭምር የሚጠይቁት በመሆኑ ለቤተሰቡ ለግል ሀብቱ ከባድ አደጋ ሲሆን ለእዳ ጠያቂዎች ግን ዋስትና እና ጠቃሚነት ያለው ነው። ነጋዴው ሲሞት ንግዶ ከንግድ መዝገብ የሚለይ ሲሆን ወራሾች ካሉ በውርስ ማጣራት ሂደት የሚከናወን ሲሆን የገንዘብ ጠያቂዎችን ከንግዱና ከውርሱ ሀብቱ እዳ ከከፈሉ በኋላ ላይ ለራሳቸው የሚወርሱ ይሆናል።

6. የጹሁፉ መደምደሚያ እና የህግ ምክር

የግል ንግድ እና ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሁለቱም ጋር የአንድ ሰው ሀብት ሲሆኑ ከኃላፊነት ፣ ህጋዊ እንቅስቃሴ እና ውጤት አንጻር የራሳቸው የሆነ ጸባይ ያላቸው በመሆኑ ቀድሞ በማጤን የህግ ባለሙያ በማማከር እንደ ባለሀብቱ የሀብት አቋም እን የንግድ ፍላጎት አንጻር መመስረት ፣ ሊመጣ ከሚችለው ኪሳራ እና ጉዳት በመጠበቅ ለታለመለት የንግድ ትርፍ ሊረዳ የሚችል ነው።

ማጣቀሻዎች/References/
1. የንግድ ህግ አዋጅ ቁጥር 1243/13
2. ፍቃዱ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ የህግ ኩባንያ 3ኛ እትም
ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው
0929101037,0983337690


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2