በጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን ምስክርነት መጠቀም ተከለከለ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሕክምና ተቋማት ከዚህ በኋላ በሚያወጧቸው ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን የሕክምና ምስክርነት ማካተት እንዳይችሉ እገዳ ተጣለ።

ይህ የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ አዘገጃጀትና ሥርጭት መመሪያ ቁጥር 1134/2018 ተገቢ ያልሆኑ የማስታወቂያ አሠራሮች በኅብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እየፈጠሩ በመሆኑ የሕዝብን የሥነምግባርና የባህል እሴቶችን ለመጠበቅ የወጣ ነው።

መመሪያው በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በድረገጾች፣ በቢልቦርዶችና በታተሙ ቁሳቁሶች ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን በሙሉ ይመለከታል።

አዲሱ ሕግ በጤና ማስታወቂያዎች ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በሙሉ አገልግሎቱን በትክክል ያገኙ መሆን እንዳለባቸውና አስቀድመው በጽሑፍ ስምምነት መስጠት እንዳለባቸው ያስገድዳል።

ተሳታፊዎቹ ሕፃናት፣ የአእምሮ ጤና እክል ያለባቸው ወይም በራሳቸው መወሰን የማይችሉ ወገኖች ከሆኑ ደግሞ ከወላጅ ወይም ከሕጋዊ አሳዳጊ የጽሑፍ ፈቃድ ማግኘት ግዴታ ሆኗል።

ይህንን ድንጋጌ በመጣስ ያለፍቃድ ወይም አገልግሎቱን ያላገኘን ሰው ምስክር አድርጎ የተጠቀመ ተቋም ከ20 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ሕፃናትንና ውሳኔ መስጠት የማይችሉ ሰዎችን ያለ ሕጋዊ ፈቃድ ያሳተፈ ተቋም እስከ 100 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይጠብቀዋል።

የተጣለውን አስተዳደራዊ ቅጣት በሦስት ወር ውስጥ የማይከፍሉ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀታቸው እንዲታገድ ይደረጋል።

በተጨማሪም መመሪያው ለማስታወቂያ አሰራጮች እና ለሚዲያ ተቋማት አዲስ ኃላፊነት ጥሏል።

ማስታወቂያዎችን የሚያስተላልፉ አካላት ይዘቱ መመሪያውን ያሟላ እና ትክክለኛ መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ሕጉን የጣሰ ማስታወቂያ ያስተላለፈ የሚዲያ ተቋም ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከ10 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ብር ሊቀጣ ይችላል።

ይህ ክልከላ በብዙኃን መገናኛዎች፣ በትራንስፖርት ላይ በሚለጠፉ፣ በሹራቦች፣ በራሪ ወረቀቶችና በቢልቦርዶች ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎችንም ይጨምራል።

ማስታወቂያዎች የሀገሪቱን የጤና ፖሊሲ ያከበሩ፣ ከልክ ያለፈ የሙያ ቃላትን የማያበዙና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ቋንቋ የሚዘጋጁ መሆን አለባቸው።

በተለይም የመጀመሪያው ምርጫ፣ የሁሉም ምርጫ እና የመሳሰሉ አባባሎችን መጠቀም ሙሉ በሙሉ የተከለከለ ሲሆን፣ ተቋማት ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ አድርገው ማቅረብ ወይም የእነሱ ባለሙያዎች ብቻ ልዩ ችሎታ እንዳላቸው አድርገው መናገር አይችሉም።

እንዲሁም ከአንድ ተቋም ሕክምና ካላገኙ አደጋ ሊገጥም እንደሚችል የሚያስፈራሩ ወይም በስሜት ላይ የሚያሴሩ የማስታወቂያ ይዘቶች የተከለከሉ ሲሆን፣ ተቋማት ያገኟቸውን ሽልማቶች በማስታወቂያ ላይ ማካተት የሚችሉት የሽልማቱን ዘመን፣ ምክንያቱንና ሰጪውን አካል በትክክል ሲገልጹ ብቻ መሆኑ ተደንግጓል።

#health #ministryofhealth #law #media #advertising #directive #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2