የአርቲስት ነፃነት አባት ወርቅነህ ዕምሩ የተወለዱት በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶኮ ሎሻ ቀበሌ ልዩ ስሙ አፋ ጉታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
ሻምበል ወርቅነህ ዕምሩ በልጅነታቸው ወደ አዲስ አበባ ለሽመና ስራ የሄዱ ሲሆን በደርግ ዘመነ መንግስት ሃገራቸውን በውትድርና ሲያገለግሉ እንደነበሩም ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
ከውትድርና መልስ በአዲስ አበባ ፖሊስ ውስጥ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት ሻምበል ወርቅነህ ዕምሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ ዘርፍ ለዓመታት ማገልገላቸውንም የመረጃ ምንጮቻችን ነግረውናል።
ሻምበል ወርቅነህ ዕምሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያገለገሉ ሳሉ ባደረባቸው ሕመም በአዲስ አበባ ፖሊስ ሆስፒታል ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው የቀብር ስነስርዓታቸው በቀጨኔ መድኃኔዓለም መፈፀሙንም ገልፀውልናል።
የሻምበል ወርቅነህ ዕምሩ ስርዓተ ቀብር አዲስ አበባ ከተፈፀመ በኋላ የለቅሶ ስነ-ስርዓት በትውልድ አካባቢያቸው በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶኮ ሎሻ ቀበሌ ወዳጅ፣ ዘመዶቻቸው በተገኙበት መከናወኑን ሰምተናል።
ተወዳጁ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ባጋጠመው ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ስርዓተ ቀብሩ በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መፈፀሙ ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ በክፍለሀገር የሚገኙ የአርቲስቱ አባት ቤተ ዘመዶች የአርቲስት ነፃነት ወርቅነህን ለቅሶ ዕርማችንን እናውጣ በማለት በጠየቁት ጥያቄ መሠረት የአርቲስት ነፃነት ወርቅነህ የለቅሶ ስነ-ስርዓት በአባቱ ትውልድ ሃገር በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶኮ ሎሻ የነፃነት ወርቅነህ ወንድም ወንደሰን እና እህቱ መሰረት በተገኙበት በባህላዊ ስነስርዓት ተከናውኗል።
የአርቲስት ነፃነት አባት ሻምበል ወርቅነህ እምሩ ከሃገር ቤት ከወጡ ከ60 ዓመት በላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ልጆቻቸውን ጋሞ ዞን ከሚገኙ ቤተ ዘመዶቻቸው ጋር ሳያስተዋውቁ መቅረታቸውንም ጠቅሰዋል።
በጋሞ ባሕል በየትኛውም አካባቢ ሰው ይሙት ለቅሶ በአባት ሃገር ሳይለቀስ አይቀርም ያሉት ምንጮቻችን ለቅሶውን በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶኮ ሎሻ ቀበሌ ለማስለቀስ በተደረገው ጥረት በዛሬው ዕለት በባሕላዊ ስነስርዓት የአርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ወንድም ወንደሰን እና እህቱ መሰረት በተገኙበት በድምቀት ተከናውኗል።



Source: Yeneta Tube









No comments yet.