#Fastmereja I በሀገራችን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና የሴት ልጅ ግርዛት አስከፊነት በእውነተኛ ታሪክ ላይ መስርቶ የሚያሳይ ”ህዶቴ” የተሰኘ አዲስ ፊልም ሊመረቅ መሆኑ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።
”ህዶቴ” የወላይትኛ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “ተስፋነሽ” ማለት እንደሆነ እና ፊልሙ ማህበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አጥብቆ እንዲቃወም የማንቂያ ደውል መሆንን ያለመ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።
ለመሥራት አንድ ዓመት የፈጀውና ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ፊልም፤ 75% ቀረጻው በወላይታ ዞን እንዲሁም 25% በሀዋሳ ከተማ የተከናወነ ሲሆን ፊልሙ ለዓለም አቀፍ ዕይታ እንዲበቃ በእንግሊዘኛና በጀርመንኛ ቋንቋዎች የፅሁፍ ትርጉም (Subtitle) የተደረገለት መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ታላቅ ስራ ላይ እነ ፅናት ተረፈ፣ ሄኖክ አለማየሁ፣ አማኑኤል የሺወንድ እና ናርዶስ አንትዋ ያሉ ተዋንያንን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ215 በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል።
ፊልሙን ከዚህ ቀደም ”ጀቢና” እና ”ጋዜጠኛዋ” የተሰኙ ፊልሞችን ያዘጋጀው ሳሙኤል ተሻገር (የእማዬ ልጅ) የደረሰውና የመራው ሲሆን፤ ታምራት በርሄ ደግሞ በኤግዚኪዩቲቭ ፕሮዲውሰርነት ሰርቶበታል፡፡
ፊልሙ ከአድዋ ሙዚየም ምረቃ በኋላ በዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎችና በሀገር ውስጥ ሲኒማዎች ለእይታ የሚበቃ ሲሆን፤ በአውሮፓ ለማሰራጨትም ከጀርመኑ ”ግሩምበርግ ፊልም” (Grümberg Film) ኩባንያ ጋር የ3 ዓመት ስምምነት መፈጸሙ ተነግሯል።
የቀለም ፊልም ፕሮዳክሽን ስራ የሆነው ይህ ፊልም፤ በመጪው ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 11ሰአት ጀምሮ በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም (ፓን አፍሪካ አዳራሽ) እና በጀርመን ፍራይቡርግ ከተማ በተመሳሳይ ቀን በድምቀት እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ ገልፀዋል።



Source: FastMereja









No comments yet.