በኤፍሬም የማነ
#Ethiopia | አርሰናል በሆነው ባልሆነው ይጨነቃል ። አርሰናል በልጦ በተቆጣጠረው ጨዋታም ይጨነቃል ። ለወረደውም ለረባው ላልረባውም ያምጣል ይጨነቃል ። በጊዜ ጨዋታ ማጠናቀቅ በመድፉ ቤት ብርቅና ድንቅ ነው ። አርሰናል ለአደጋ እራሱን እንደጋበዘ ለዛሬ የከፍታ ደረጃው በርካታ ውድ ሶስት ነጥቦችን ከያዘባቸው ጨዋታዎች መሃከል አንዱ የበርንሌይ ፍልሚያ ሆኗል ። ማይክ አርቴታ ዛሬም የአርሰናል ዋና አሰልጣኝም ዋና ተጋጣሚም መስሎ የወረደው በርንሌይን በቆመ ኳስ ጎሉ 1ለ0 ረቷል ። የመድፉ የዛሬ ከፍታ ዋና ተዋናይ አርቴታ በምሽቱ ጨዋታ ዋና አጥቂው ዮኬሬስን ከካይ ሃርቫርትዝ ለምን በቋሚነት እንዳላስጀመረ አይታወቅም ። አርቴታ ኦዴጋርድ እና ኤዜን በጋራ ሲጠቀም ዮኬሬስን ተጠባባቂ ያደርጋል ። ኦዴጋርድ እና ኤዜን ቤንች ያደረገ ዕለት በአንፃሩ ዋና አጥቂው ዮኬሬስን በቋሚነት ያለ አቅራቢዎቹ ያሰልፋል ። ይህ የማይክ አርቴታ አባዜ ለሁለም መነጋጋሪያ ሆኗል ።
በጨዋታው የተሻለው ቡድን በጊዜ ጨዋታውን መግደል እንደልማዱ እንደተሳነው በድል ፈፅሟል ። የቆመ ኳስ ዛሬም መድፉን አድኗል ። የጎሉ ባለቤት ካይ ሃርቫርትዝ 68 ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ያልተባረረው በዳኛው ችሮታ ሆኗል ። በልጦም ተበልጦም በሜዳውም ከሜዳው ውጭም ከተረፈውም ከወረደውም በሆነውም ባልሆነውም ጨዋታ ሁሉ በጊዜ ጨዋታን ማጠናቀቅ ለመድፈኛው ብርቅና ድንቅ እንደሆነ የሰሜን ለንደኑ ገናና ለሚመጥነው የሻምፒዮንነት ንግስናው ተቃርቧል ። አርሰናል በብዙ የአንድ ሻምፒዮን ቡድን የጥንካሬ መልኮች መዋቅር ከየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ጠንካራው የተከላካይ መስመር ቅኝቱ ጋር በታላቁ ፔፕ ጋርዲዮላ የስንብት ዋዜማ ወደ መጨረሻው ክብር ከመቼውም ግዜ በላይም ተጠግቷል ። የመድፉ የፀና የድል አሸናፊነት ጉዞ ዋና የውድድር ዓመቱ የጥንካሬ መለያ ቢሆንም አርሰናል ከአናት እየመራው በዘለቀው ገናና ሊግ ከህልሙ ጫፍ ለመድረስ የተሟላ የቡድን ጥልቀት የተጨዋቾች አማራጭ ይዞ በሁሉም የጨዋታ ቅርፆች ለወራጁ ሁሉ እላፊ መጨነቁ የበለጠውን ጨዋታ በጊዜ ለመግደል መቸገሩ ግን አጠያያቂ ነው ።
በሊጉ ብቻ በ22 ጨዋታዎች ለ18ኛ ጊዜ ከቆመ ኳስ የተቆጠረችው የካይ ሃርቫርትዝ ብቸኛ ጎል መድፈኛውን ለ22 ዓመት ከራቀው ታላቅ የዋንጫ ክብር ለማገናኘት የመጨረሻው መጨረሻ ቀጠሮው ይጠበቃል ። ምናልባትም የመድፉ የውድድር ዓመቱ በጭንቅ የቀጠለ ልፋት ነገም ከቫይታሊቲ ስቴዲየም የሲቲ በርንማውዝ ፍጥጫ ጋር ሊጠናቀቅ ሊፈፀም ይችላል ። ካልሆነ ግን ለተናፈቀው ዋንጫ ልጅን ከመድፉ መንደር ለማንሳት ምጡ መጨነቅ መንቆራጠጡ እስከ 38ኛው ሳምንት የሲዝኑ ፍፃሜ አሰልጣኝ ማይክ አርቴታ አንዴ አሸንፎ እስካልተገላገለ ድረስ መቀጠሉ ለመድፉ ወዳጆች ሁሉ ዕርግጥ ነው ።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.