ምርጫው ውጤቱ ከሞላ ጎደል ቢታወቅም መሠረታዊ ሂደቱና ቅድመ ኹኔታዎቻችንን ቸል አንልም!

- Advertisement -
Sidebar AD

– በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ

የአገራችን ሠላምና መጻዒ እድል ሊወሰን የሚችለው በእውነተኛ በኾነ የሕዝብ ተሳትፎ እንጂ የይስሙላ በሚደረግ ምርጫ እንዳልኾነ ትብብራችን ቀደም ሲል በገለጸውና አኹንም በያዘው ጽኑ አቋም መኾኑ በጽኑ ያምናል። ገዢው ፓርቲ በየደረጃው በሚገኙ የጥርነፋ መዋቅሮቹ አማካኝነት የሕዝብን ነጻ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጨፍለቅና የምርጫውን ሂደት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እያደረገ ያለው ሕገ ወጥና አምባገነናዊ ተግባር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥር ሰዶ ታይቷል። በተለይ ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ አፈናውም ኾነ ማዋከቡ እየጨመረ ሲኾን ክልከላውም እየበዛ ይገኛል።

ትብብራችን ከዕጩዎች ምዝገባ ጀምሮ ቅድመ ምርጫ ሂደት ላይ የታዘባቸውንና በማስረጃ ማስደገፍ የቻላቸውን ተጨባጭ የኾኑና መሬት ላይ ያሉትን አስደንጋጭ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ ማድረግ እንዳለበት ያምናል። አብዛኞቹ ክስተቶች ለቦርዱ ሪፖርት የተደረጉና መፈታት የሚቻሉ ቢኾንም ሣይፈቱ የቀሩ በተለይም በቦርዱ በታችኛው መዋቅር መሥራትና ማስተካከል የሚገባውን ባለማድረግ የቀረበ ነው፡፡ በዚኽም

1. በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕናና አካባቢው ባሉ ወረዳዎች በሲስተም ችግር ምክንያት ከ 15 በላይ የትብብሩ ዕጩዎች ሳይመዘገቡ በመቅረታቸው ምክንያት በትብብር ፓርቲዎች አባላት እንዲኹም አመራሮች የደረሠውና እየደረሠ ያለው የሞራል፣ የጊዜ፣ የገንዘብና የሕግ ኪሣራ ሲያስከትል በጥቅል ሲታይ መሰል ችግሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ እጅግ ጠንካራ ዕጩወቻችን ሳይመዘገቡ በመቅረታቸው ሌሎች ካለው ነባራዊ ሀቅና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የተቃረኑና የተነጠሉ ፓርቲዎች የቊጥር ብልጫ እንዲያገኙ የፈቀደ ኾኖ አግኝተነዋል። ምርጫ 2018 ከካድሬውና ከሚካሄዱ ጦርነቶች ቀጥሎ ሲስተም ዋና ችግር ኾናል።

2. በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ምርጫ ክልል ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ 92 ምርጫ ጣቢያዎች አፈጻጸማቸው በአንድ ቦታ በአንድ ድንኳን ሥር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ችግሩ መጠነ ሰፊና ከሞላ ጎደል በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል እየተደረገ ሲኾን የትብብራችንን ዕጩ የክልሉ የብልጽግና ካድሬ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና ደህንነቶች በመተባበር ከዕጩነት እንዲለቅ ወይም ምርጫ ክልል እንዲቀይር ለዚያም የስልጣን ዳረጎት እንደሚሰጧቸው በማግባባት ያን ካልፈጸሙ በሕይወት መወራረድ እንደኾነ ዛቻ ተፈጽሞባቸዋል። በዚኽም ሳይበቃ በሥራ ቦታ፣ በቤተሰቦቻቸው ላይ ግልጽ ዛቻ ተፈጽሟል። ዕጪው በኦሮምኛ ክርክሮች ትልቅና ዐይን ገላጭ አመክንዮ ያቀርቡ የነበሩ በመኾናቸው አንዱ ዛቻ በክርክር ወቅት ኮሪደር ልማቱን አንቋሸህና አሳንሰህ ተናግረሃል የሚል ነው።

3. በጸጥታ ሥጋትና በምርጫ አስቻይነት ላይ ወደክልሎች በመንቀሳቀስ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በደቡብና በቤኒሻንጉል የተንቀሳቀሰው ፓርቲዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጣው ቡድን የተሻለና መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የተቀራረበ ሪፖርት ያቀረበ ሲኾን በአንጻሩ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተንቀሳቀሰው ቡድን 97% በላይ አስቻይ ኹኔታ አለ በሚል የተዛባና አሳሳች ሪፖርት ለቦርድ አቅርቧል። በትብብራችን ግምገማ አማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ወይም በጣት የሚቆጠሩ ከተሞች ካልኾነ ለምርጫ አስቻይነት ኹኔታ የለም። በኦሮሚያ ክልል ከፊሉ ወይም ከዋና ዋና ከተሞች ወጣ ብለው ባሉ አካባቢዎች ፍጹም አስቻይ ኹኔታ እንደሌለ እንረዳለን። ስለኾነም የኹለቱ ክልሎች የጥናት ውጤት ውድቅ ነው፤ቦርዱም ሕዝብም እንዳይቀበለው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

4. የመራጮችን መረጃ ምንተፋ፣ ሥነልቡናዊ ጫናና ማዋከብን በተመለከተ፣
ምርጫ ካርድ ያልወሰደ ዜጋ ማንኛውንም የመንግሥት አገልግሎት እንዳያገኝ መከልከል፣ ገበሬው ማዳበሪያ ለመውሰድ በቅድሚያ የምርጫ ካርድ መውሰድ መሥፈርት የነበረ ሲኾን ከምዝገባ ማግስት ደግሞ መራጮች ልዩ የመራጭነት መለያ ኮድ፣ ስልክና ፋይዳ ቁጥር በግድ እንዲያስመዘገቡ ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል። ትብብራችን ባደረገው ዳሰሳ መሠረት በተለይ የመንግሥት ሠራተኞች በኃላፊዎቻቸው በኩል እንደ ንግድ ባንክና መሰል የአገልግሎት ተቋማት በይፋ ቅጽ በማስቀመጥ ከአገልግሎቱ በፊት ሙሉ መረጃውን እንዲሞላ በማድረግ፣ ካድሬው በፖሊስና ሚሊሻ በመታገዝ በየቤቱ በመግባት የመራጮችን ካርድ ፎቶ በማንሳት፣ ገለልተኛ መኾን የነበረበት የጸጥታ አካላት ለካድሬው አግዘው መራጮችን ማዋከብና ማሰር፣ ኮድ በመመዝገብና ምርጫቸውንም በመወሰን በሚመስል አኳኋን በተለይ በአዲስ አበባ ተፈጽሟል። ከዚኹ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ያሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች የታብሌት መረጃዎችን አሳልፈው እንዲሰጡ ጫና ደርሶባቸዋል፤ ማባበያም ቀርቦላቸዋል። በአማራ ክልል ያሉ አስፈጻሚዎች ብልጽግና ቢያሸንፍም ባያሸንፍም አሽንፏል ብላችሁ ታውጃላችሁ ለዚያም ዳረጎት አላችሁ በሚል እንደተዋከቡ መረጃዎች ደርሰውናል።

5. ለአንድ ግለሰብ ኹለትና ከዚያ በላይ ካርድ መስጠት።
በአማራ ክልልና ሌሎችም አካባቢዎች አንድ መራጭ እስከአምስት ካርድ እንዲወስድ ተደርጓል። ትብብራችን ባደረገው ማጣራት አንድ ግለሰብ ኹለት ካርድ የወሰዱበት እጃችን ይገኛል።

6. ለመራጭነት ለመመዝገብ የሄዱ ሰዎች በዚኽ ፋይዳ ሌላ ካርድ ወጥቶበታል በሚል ተመልሰዋል። በተመሳሳይ ዜጎች የወሰዱትንም የመራጭነት ካርድ ሰብስበው ለብልጽግና አመራሮች እንዲያስረክቡ መደረጉ፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ኮሚቴዎች ከነዋሪው ገንዘብ አሰባስበው ለምርጫ አስፈጻሚዎች የምሳና የእራት ግብዣ እንዲያደርጉ መገደዳቸው።

7. በሐረር ከተማ፣ ጀጎል ምርጫ ክልል የክልሉ መንግሥት ሐደሬ ካልኾኑ መወዳደር አይችሉም በሚል ባቀረበው አቤቱታ የትብብራችን ዕጩ ተሰርዘዋል። ይኽም ጥቁር በጥቁር ላይ የፈጸመው አፓርታይድ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

8. በኦሮሚያ ክልል በግል ተቋማት ላይ ለብልጽግና ምርጫ ቅስቀሳ አዋጡ በሚል ግዳጅ በመጣል በርካታ ሚሊዮን ብር ያለ ደረሰኝ ተሰብስቧል።

9. በቦርዱ የተዘጋጀውን ምርጫ ክርክርና የተቃዋሚዎችን ተከራካሪዎች አድንቀው በማኅበራዊ ትሥስር ገጻቸው ያጋሩ ግለሰቦች እየታደኑ እየታሠሩ ይገኛል።

10. ገዢው ብልጽግና የአባቱ ኢሕአዴግን ርካሽ ተግባር በመውረስ ሕብረተሰቡን 1ለ5 እና 1ለ10 መጠርነፍ ማስፈራራት።

11. በሕግም በሞራልም ከፖለቲካ ፍጹም ንክኪ እንዳይኖረው በሚል ከዓለም ባንክና መሰል ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት የገንዘብ ምንጭ የሚላስ የሚቀመስ ላጡ ወገኖቻችን ለመርዳት የሚተገበረውን የሴፍቲኔት ፕሮግራም በተረጂዎች ችግር በመግባት ፖለቲካዊ ብዝበዛ ማካሄድ።
እነዚኽ ውጤቱን በመሠረታዊነት የሚቀይሩ ኾነው ያገኘናቸውን ገለጽን እንጂ ከቦርዱ ጋር በየቀኑ የምንለዋወጣቸውንና የተፈቱትን ካነሳን መጽሐፍም አይበቃ።
ስለኾነም፣

ገዢው ብልጽግና፣
በአጠቃላይ ገዢው ብልጽግና በተለይ አስቻይ ኹኔታ ባለባቸው አዲስ አበባ፣ ሦስቱ የደቡብ ክልሎች፣ ድሬዳዋና ሐረር ባሉ አካባቢዎች ራሱን እንዲገራና ትብብሩ ምንም እንከን የማይታገስ መኾኑን።
በትብብሩ ለምርጫ አስቻይነት የቀረቡ ጦርነት ማቆም፣ የፖለቲካ እሥረኞችን መልቀቅ፣ ምኅዳሩን ማሻሻል እና ከእውነተኛ ተቃዋሚው ኃይል፣ ልኂቃንና መሑራን ጋር ኹሉን አቀፍ ድርድር መጀመር የመሰሉ አኹንም
ሳይውል ሳያድር እንዲጀምርና እንዲፈጽም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። በሚታዩ የካድሬው የበዛ ነውሮች ላይም እርማጃዎችን ወስዶ በይፋ ለሕዝብ እንዲገልጽ እንጠይቃለን፡፡

መንግሥት ለእነዚኽ መሠረታዊ ጥያቄዎቻችን እንዳለፈው ጊዜ ኹሉ በጆሮ ዳባ ልበስ ምንም ተግባራዊ እርምጃ ካልወሰደ የምርጫ ተሳትፏችን እንደገና ልናጤነው እንደመንገደድ ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ቦርዱ፣
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለይ ከፍተኛ አመራሩ በጠባቧ ቀዳዳ እያደረገ ያለው ጥረት ምሥጋና ያለን ሲኾን የአባላት ደህንነት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ። የበለጸገው ሲስተም ከዚኽ በኋላ በየትኛውም የምርጫ ሂደት ውስጥ ጥቅም እንዳይኖረው እንዲያግድ እናሳስባለን።

ሕዝቡ፣
ካድሬው በተለያየ መልኩ ሊያስፈራራውና ሊያዋክበው ቢሞክርም ድምጽ ሲሰጥ ከፈጣሪ በታች ማንም እንደማያየው ማወቅ አለበት፤ ለዚያም ትብብሩ ከጎኑ ይቆማል። በዚኹ አጋጣሚ ለምናደርገው ሰላማዊ ትግል ጥሪ ዝግጁ እንዲኾን እናሳስባለን።

በትብብር ከገጠመን የሕልውና አደጋ እንዳን!

ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት – ለኢትዮጵያ
ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2