ከ17 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ መሣሪያ ለማግኘት በወረፋ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

- Advertisement -
Sidebar AD

በሀገሪቱ በሚገኙ 18 የተሐድሶ ማዕከላት ውስጥ ከ17 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ መሣሪያ ለማግኘት ተመዝግበው በወረፋ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ ጉጆ እንደገለጹት፤ “የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት” የተሰኘው ማዕከል ከተቋቋመ በኋላ እስካሁን ለ2 ሺህ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ መሣሪያ ማቅረብ ተችሏል። ይሁን እንጂ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር በሀገሪቱ ያለው የአካል ድጋፍ መሣሪያ አቅርቦት ከ7 በመቶ እንደማይበልጥ ተናግረዋል።

አንድ አካል ጉዳተኛ አርቴፊሻል እግር ለማሰራት ቀጠሮ ተይዞለት እስከ 6 ዓመት ድረስ ለመጠበቅ እንደሚገደድ በመግለጽ ያለውን የአቅርቦት እጥረት አስረድተዋል።

“የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት” የተሰኘው ማዕከል በ2016 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ በኋላ አርቴፊሻል እግር፣ እጅ፣ ዊልቸር እና ክራንች በማምረት ለአካል ጉዳተኞች እያቀረበ ይገኛል፤ በተጨማሪም መስማት ለተሳናቸው የማዳመጫ መሣሪያ፣ ለዓይነ ስውራን ደግሞ ነጭ በትር እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ይህንን ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነቶችን በመፈጸም በየሦስት ወሩ 300 ዊልቸሮችን እያደለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በአካል ድጋፍ መሣሪያ እጥረት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎችና የከፋ ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎች እንደሚገኙበት ገልጸው፤ የተገጠመላቸው አርቴፊሻል እጅና እግር ከእድገታቸው ጋር ባለመመጣጠኑ ምክንያት ቅያሬ የሚፈልጉ አካል ጉዳተኞች ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነ አክለው ገልጸዋል።

በ ሙሉጌታ በላይ


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: