#Fastmereja I ኢትዮጵያ በሕክምና ምርምርና ክሊኒካዊ ሙከራዎች (Clinical Trials) ያላትን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና የቁጥጥር ሥርዓቷን ዘመናዊ ለማድረግ ያለመ አዲስ የዲጂታል መረጃ ሥርዓት በይፋ ሥራ አስጀመረች።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) ይፋ ያደረገው ይህ የኦንላይን ሥርዓት፣ ቀደም ሲል በወረቀትና በአካል ንክኪ ይከናወን የነበረውን የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ሂደት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚተካ ነው።
ይህንን አዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ይፋ ለማድረግና ተያያዥ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክን ለመክፈት በተዘጋጀው ታላቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ፍሬህይወት አበበ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ተመራማሪዎች፣ የአካዳሚክ ማኅበረሰብ አባላትና የስፖንሰር ተወካዮች ተገኝተዋል።
አዲሱ ሥርዓት ተመራማሪዎች ባሉበት ሆነው በኦንላይን እንዲያመለክቱና የጉዳያቸውን ደረጃ በቀጥታ (Tracking) እንዲከታተሉ የሚያስችል ሲሆን ከዚህም ባሻገር ፈቃድ ከተሰጠ በኋላም ቢሆን የደኅንነት (Safety) ሪፖርቶች፣ የጂሲፒ (GCP) ኢንስፔክሽን መረጃዎች እና ተያያዥ ግብረ‐መልሶች በጥብቅ የቁጥጥር ሰንሰለት ውስጥ እንዲያልፉ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ፍሬህይወት አበበ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳመለከቱት፣ ድንገት የሚከሰቱ ወረርሽኞች፣ የፀረ-ተህዋሲያን መላመድ (Antimicrobial Resistance) ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በወቅቱ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ማመንጨት የሚችል ጠንካራ የሕክምና ሙከራ ምርምር አቅምን ይሻል ሲሉ ገልፀዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለዉም ይህ ሥርዓት ጊዜን፣ ወጪን እና ጉልበትን በመቆጠብ ረገድ የጎላ ሚና እንዳለዉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሕክምና ሙከራ ሥርዓቷን በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ለማሟላት ባደረገችው መጠነ-ሰፊ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ፣ በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የሕክምና ሙከራ የቁጥጥር ሥርዓት የብስለት ደረጃ 3 (Maturity Level 3 – ML3)ማግኘት መቻሏ በዕለቱ ተገልጿል።
ቀጣዩ ግብ ባለሥልጣኑን የልህቀት ማዕከልና የብስለት ደረጃ ወደላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።
ባለሥልጣኑ ማንኛውም በሰው ልጅ ላይ የሚደረግ የሕክምና ወይም የመድኃኒት ሙከራ ከባለሥልጣኑ ይፋዊ ፈቃድ ውጪ ሊጀመር እንደማይችልና ያለ ፈቃድ የሚከናወኑ ማናቸውም ሙከራዎች በሕግ “ሕገ-ወጥ” ተብለው በጥብቅ እንደሚቀጡ አስገንዝቧል።
አዲሱ ሥርዓት የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋራ ድጋፍ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።



Source: FastMereja









No comments yet.