የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ለማዘመን የ700 ሚሊዮን ብር የልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FasfMereja I ​የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅን በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ለማዘመን መታቀዱ ተገለጸ። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እና ግሪን ቪው አሊያንስ ከተባለ ሀገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በተዘጋጀ መድረክ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተገኝተዋል።

​መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ ሻምበል፣ ዞኑ በውብ ተፈጥሮ፣ በብዝሃ ባህልና በህብረ ብሔራዊነቱ የሚታወቅ የኢንቨስትመንት ኮሪደር መሆኑን ገልጸዋል። አካባቢው የቡና፣ የቅመማ ቅመም፣ የማር፣ የፍራፍሬና የወርቅ ማዕድን መገኛ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ የኮሌጁ መዘመን ለቀጣናው የግብርና ልማትና ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

​የኮሌጁ ዲን አቶ ካሳሁን ናይክ የኮሌጁን ታሪክና ይፋ የተደረጉትን የ700 ሚሊዮን ብር የልማት ፕሮጀክቶች ዝርዝር ማብራሪያ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። ኮሌጁ በ1995 ዓ.ም የተመሰረተና የ23 ዓመት ዕድሜ ያለው አንጋፋ ተቋም ሲሆን፣ በሀገሪቱ ካሉ 5 ቀዳሚ የግብርና ኮሌጆች አንዱ መሆኑን ዲኑ አስታውቀዋል። ተቋሙ እስካሁን ከ7,000 በላይ የግብርና ልማት ሰራተኞችን (DAs) አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዕፅዋት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በእንሰሳት ሳይንስ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። በቀጣይም የእንስሳት ጤና ህክምና ትምህርት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

​ኮሌጁ የስልጠና ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ በራሱ አቅም ገቢ የሚያስገቡ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በስፋት ማከናወን መጀመሩ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ከ52 በላይ የወተት ላሞችን ለማርባት የሚያስችል ዘመናዊ ማዕከል እየተገነባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ25 በላይ የሚሆኑት ምርት መስጠት ጀምረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ የወተት ማቀነባበሪያ ስራ ድርጅት በሂደት ላይ ይገኛል። በዶሮ እርባታ ዘርፍም በአሁኑ ወቅት 9,000 የዶሮ ዝርያዎች ያሉት ሲሆን፣ ከዚህ ዘርፍ ከ1.2 ሚሊዮን እስከ 19 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል። የዶሮ ስጋ እና የወተት ምርቶችን በቀጥታ ለተጠቃሚው ለማቅረብ የሚያስችል ሱፐርማርኬትም እየተገነባ ሲሆን፣ በንብ እርባታው በኩል ከ300 በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በመጠቀም የማር ምርት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው።
​የኮሌጁን ቀጣይ ስትራቴጂካዊ ጉዞ ለማሳካት ከተመደበው የ700 ሚሊዮን ብር በጀት ውስጥ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል የቡና እና ሻይ ስልጠና የላቦራቶሪ ግንባታ፣ የሴት ተማሪዎች ማደሪያ (ዶርሚተሪ)፣ ዘመናዊ ኩሽና፣ የኮሌጁ ዋና መግቢያ በር እና የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ማስተካከያ ስራዎች ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ለኮሌጁና ለከተማው ማህበረሰብ የሚያገለግል ዘመናዊ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና ንፁህ ውሃ ለማቅረብ የሚያስችል ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ታውቋል።

​የ”ግሪን ቪው አሊያንስ” መስራችና አምባሳደር ሚካኤል ነጋሳ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው በሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በንቃት መሳተፉን አስታውሰዋል። ባለፉት 7 ዓመታት በመንግስት አነሳሽነት 42.5 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውንና ይህም የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 27.5 በመቶ ማሳደጉን ጠቅሰው፣ ይህ የኮሌጁ የማዘመን ጉዞም ለዚሁ አረንጓዴ ልማትና ለአርሶ አደሩ ምርታማነት ማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1