በትግራይ ትምህርት ቤቶች በደመወዝ እና ሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ግንቦት 30 ሊዘጉ ነዉ

- Advertisement -
Sidebar AD

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከነዳጅ እጥረት፣ ከደመወዝ መዘግየት እና ከትምህርት መሠረተ ልማት መስተጓጎል ጋር በተያያዘ ምክንያት ከታቀደው አንድ ወር ቀደም ብሎ እንደሚያበቃ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ ጉሽ የፌደራል መንግሥት የበጀት ድልድል እና የነዳጅ አቅርቦቶችን መከልከሉ በክልሉ «የመምህራን ደሞዝ በወቅቱ እና በአግባቡ መክፈል» የማይቻል አድርጎታል ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል።

የክልሉ የትምህርት ቢሮ ፤ ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠቱን ለዶቼ ቬለ የተናገረዉ በመቀሌ ነዋሪ የሆነዉ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አፅብሃ ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች የ 2018 የትምህርት ዘመን ግንቦት 30 እንዲዘጋ ወስኗል። ትምህርት ቢሮዉ ለዚህ ምክንያት የሰጠዉ አንደኛ -የፌደራል መንግሥት በጀት እየላከ ባለመሆኑ ፤ ሁለተኛ ፤ መምህራን ደሞዝ እያገኙ ስላልሆነ ሥራቸዉን እየለቀቁ በመዉጣታቸዉ ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ በመሆኑ ነዉ ሲል አክሏል። ወላጆች ልጆቻቸዉን ትምህርት ቤት የሚያደርሱበት ነዳጅ ባለማግኘታቸዉ የግል ትምህርት ቤቶች እንዲሁ ፤ ግንቦት 30 ቀን እንዲዘጉ ተወስኗል። ለ12 ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ግን እንደሌሎች ክልሎች ሁሉ በትግራይ ክልልም ተማሪዎች በተመሳሳይ ቀን ለፈተና ይቀመጣሉ።

ይሁን እና ይህን የትግራይ ክልል የትምህርት ቢሮ መግለጫ የሰሙ የክልሉ ነዋሪ፤ ተማሪዎቹ ትምህርታቸዉ ቀደም ብሎ እንዲዘጋ የተወሰነዉ፤ ምናልባት በትግራይ ክልል እና በፊደራል መንግሥት መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ዉስጥ ገብቷል ሲል ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አፅብሃ ለዶቼ ቬለ DW ገልጿል።

ባለፈዉ ሳምንት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) መካከል የነበረዉ ዉዝግብ ሰሞኑን ረገብ ያለ መስሏል። አዲስ የተሰማ ነገርም የለም ሲል ጋዜጠኛዉ አክሎ ለዶቼ ቬለ ተናግሯል።

DW Amharic




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: