“ታሪክን ለትውልድ የማሻገር ተራው የእኔ ነው” በሚል መርህ እየታደሰ የሚገኘው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቂያ ኢትዮጵያውያን እንዲተባበሩ ጥሪ ቀረበ።
በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት የሚገኘው ታሪካዊው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከተቆረቆረ 130 ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ልዩ እና በሥነ ሕንጻ ቅርጹ በልዩ ሁኔታ የተገነባ ድንቅ የሆነ ታሪካዊ ቅርስ ነው።
ግንቦት 14 ቀን 2018 ዓ.ም የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ክብሩ ገብረ ጻድቅ እንደገለጹት ቤተክርስቲያኑ ዕድሳት ሥራ እየተከናወነ ቢገኝም ሥራው ከሚፈልገው ከፍተኛ ገንዘብ አንጻር በቂ የገንዘብ አቅም በማስፈለጉ ከግንቦት 28-30 ቀን 2018ዓም ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የበይነ መረብ (የኦንላይን) የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር መታቀዱን ገልጸዋል።
ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በተጓዘባቸው ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ያልተቋረጠ መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ የቆየ ሲሆን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ምክንያት አደጋ እየተጋረጠበት በቀደሙ አባቶቻችን ጥገና እና እድሳት እየተደረገለት በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ቢደርስም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን፣ በውስጣዊ ግንባታው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተከሰተ የውሃ ሥርገት፣ በውጫዊው ገጽታው ላይ የመወየብ እና የመሰንጠቅ አደጋ ያለምንም ብረት እና ተጨማሪ ድጋፍ በተሠራው ልዩ “የእሳተ ከላ” (የቀይ ሸክላ ኮርኒስ) ግንባታው የመሰንጠቅና የመሸሽ ሁኔታ መፈጠሩ፣ ከላይ ከጉልላቱ ጀምሮ ዝናብ በማስገባትና የውስጥ ግድግዳዎቹም በመሰነጣጠቃቸው ምክንያት ዕድሳቱ መደረጉን ገልጸዋል።
በመልአከ ገነት እንዳብራሩት የበይነ መረብ (ኦንላይን) መርሐ ግብር ከ250-300 ሚሊየን ብር ገቢ ለማሰባሰብ የታሰበ ሲሆን በዚህ መርሐ ግብር ላይ መላው ሕዝበ ክርስቲያን ቅዱስ ጊዮርጊስ ውለታ በማሰብ እና በስፋት በመሳተፍ በገንዘብ፣ በጉልበትና በአቅርቦት ክርስቲያናዊና ሀገራዊ ኃላፊነቱ እንዲወጣ አሳስበው በሁሉም ባንኮች “1423” አጭር የሒሳብ ቁጥር በመጠቀም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም የመስቀል መልሶ ማስቀመጥ መርሐ ግብርን በተመለከተ የጉልላት ሥራ በመጠናቀቁ እሑድ ግንቦት30 ቀን 2018ዓም ከቅዳሴ ውጭ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት በሚከናወነው ታላቅ የመልሶ ማስቀመጥ መርሐ ግብር ላይ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን በአካል ተገኝቶ የመስቀል መልሶ ማስቀመጥ ሂደት እንዲሳተፉና ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።



Source: FastMereja







No comments yet.