በትራንስፎርመር ላይ ስርቆትና ጉዳት ያደረሱ ወንጀለኞች እስከ 13 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ

- Advertisement -
Sidebar AD

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብና የሀገር ሀብት በሆኑ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆትና የጥፋት ድርጊቶችን ለመግታት ከጸጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።

በዚህ ረገድ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ በአበጅ ቀበሌ ውስጥ በሚገኝና በተቋማችን ንብረት በሆነ ትራንስፎርመር ላይ የስርቆትና ከፍተኛ የውድመት ወንጀል የፈጸሙ 5 ወጣቶች እስከ 13 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ግለሰቦቹ መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም በትራንስፎርመሩ ላይ ያለውን የኤሌክትሪክ መስመር በመበጠስ፣ የውስጥ ገመዶችንና ብሎኖችን በመፍታት በአካባቢው የኃይል መቋረጥና በተቋሙ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።

ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ከአካባቢው ተሰውረው የነበሩ ቢሆንም፣ የፖሊስ አባላት ከኅብረተሰቡ በደረሳቸው ጥቆማና ባደረጉት ተከታታይ ክትትል መጋቢት 6 ቀን 2018 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው ችለዋል።

ፖሊስ ያጣራውን የምርመራ መዝገብ መሠረት በማድረግ የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ባቀረበው ክስ መሠረት፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወንጀለኞቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ ጠንከር ያለ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም መሠረት ተከሳሾቹ አውላቸው ክንፈ፣ ገዛኸኝ ቢኒያም፣ መላኩ ቢረዳ እና በቃሉ አለምይርጋ እያንዳንዳቸው በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲወሰን፣ አምስተኛው ተከሳሽ በረከት ጃንጊላ ደግሞ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

የምሁር አክሊል ወረዳ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የወረዳውን ፖሊስ ዋቢ በማድረግ እንደገለጸው፣ ይህ የተላለፈው ውሳኔ በሕዝብና በሀገር ሀብት ላይ መሰል የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም በሚያስቡ አካላት ላይ ግልጽ መልእክት የሚያስተላልፍና አስተማሪ እርምጃ እንዲሆን በማሰብ መሆኑን አስታውቋል።

ተቋማችን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ከጥፋት ኃይሎች ለመጠበቅ ኅብረተሰቡ እያደረገ ላለው ተሳትፎ እውቅና እየሰጠ፣ በቀጣይም መሰል አጥፊዎችን በማጋለጥ ረገድ የምታደርጉትን ጥቆማና ክትትል አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪውን ያቀርባል።

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: