#Ethiopia | በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰብል በሽታዎችና በተባይ መከሰት ምክንያት በአርሶ አደሩ ምርታማነት ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ውድመት ለመግታት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋልና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
ይህ የተጠቆመው በዊ-ሊንክ አዘጋጅነት፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አገር አቀፍ የሰብል ጥበቃ እና ማዳበሪያ ኤክስፖ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በይፋ በተከፈተበት ወቅት ነው።
በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና የሰብል ጥበቃና የማዳበሪያ ቴክኖሎጂዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘው ይህ አገራዊ ኤክስፖ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ለአምራቾች፣ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ እስከ እሁድ ይቆያል።
በኤክስፖው መክፈቻ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና የግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ አቶ አበራ ለማ ባደረጉት ንግግር፤ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን አስታውሰው፣ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የግል ባለሀብቱና የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ሚና ምትክ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት በዘርፉ የሚታዩ የፖሊሲና የአሰራር ማነቆዎችን በጥናት በመለየት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
የመድረኩ አዘጋጅ የዊ-ሊንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ዳንኤል ገብሬ በበኩላቸው፤ እንደ የመኸር ሰብል ተባይ ፣ የበቆሎ በሽታዎች፣ የስንዴ ዋግና የቡና አረማሞ ያሉ ተከታታይ የተፈጥሮ ፈተናዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደሩትን ጫና ለመቋቋም ኤክስፖው ትልቅ መፍትሄ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህ መድረክ በባህላዊ አሰራርና በሳይንስ በታገዘ ዘመናዊ ግብርና መካከል ያለውን የቴክኖሎጂና የመረጃ ተደራሽነት ክፍተት ለማጥበብ እንደ ትልቅ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
አዘጋጆቹ አክለውም ኤክስፖው በአዲስ አበባ ቢጀመርም፣ በቀጣይ ዝግጅቶች እነዚህን ዘመናዊ የሰብል ጥበቃ፣ የአፈር ጤንነት መጠበቂያና የማዳበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ይበልጥ ወደ አምራች ገበሬው አካባቢዎች በመውሰድ በቅርበት ተደራሽ የማድረግ ሰፊ ራዕይ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
📸ከበደ መክብብ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu



Source: GetuTemesgen









No comments yet.