“ተጥለህ ነው ያገኘንህ”

- Advertisement -
Sidebar AD

በዶክተር ኃይለልዑል መኮንን (የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት)

#Ethiopia | በአብዛኞች የልጅነት ጊዜ የማይጠፋ ጨዋታ መሳይ ቀልድ አለ። “ተጥለህ እኮ ነው ያገኘንህ፤ ከጓሮ አግኝተንህ ነው እንጂ አንተ የኛ ልጅ አይደለህም።”

ሰሞኑን አንዲት ታካሚዬ የልጅነት ትውስታዋን ስታጋራኝ ይህ ንግግር ለዓመታት በውስጧ የፈጠረውን ባዶነትና የባዕድነት ስሜት ገልፃልኛለች።

ምንም እንኳን በጨወታ መሀል ወላጆች ይህን ቀልድ ቢያነሱም ለልጆች ግን የማንነት ጥያቄ የሚያስነሳ የጭንቀት ምንጭ ሊሆን ይችላል።

ህጻናት ዓለምን የሚያዩት በወላጆቻቸው አይን ነው። ወላጅ “የኛ አይደለህም” ሲል ልጁ የሚሰማው የመተው ፍርሃት እንዲሁም “እነዚህ ሰዎች ካልወለዱኝ ነገ ሌላ ሰው መጥቶ ቢወስደኝስ? ወይም እነሱ መልሰው ቢጥሉኝስ? የሚል ጭንቀት በውስጡ ሊፈጠር ይችላል።

ልጅነት “እኔ ማን ነኝ?” የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝበት ወሳኝ ወቅት እንደመሆኑ ከጓሮ ተገኘህ የሚለው ቃል ልጁን ከማንነቱ በመነጠል ራሱን ሲያይ በቤተሰቡ መሃል እንደ እንግዳ እንዲሰማው ያደርገዋል።

በእያንዳንዱ ግጭት ወይም ቅጣት ወቅት ልጁ ያንን የጓሮ ታሪክ ያስታውሳል። “የእነርሱ ስላልሆንኩኝ ነው የሚቆጡኝ” ብሎ እንዲያስብና የራሱን ማንነት እንዳይቀበል እንዲሁም ሁልጊዜ ተቀባይነት ፍለጋ እና “እኔ እዚህ ቦታ አይገባኝም” የሚል የበታችነት ስሜት ሊያሳድርበት ይችላል።

“ተጥዬ የተገኘሁ ስለሆንኩ ዋጋ እንዲኖረኝና እንዳይጥሉኝ ሁልጊዜ ሰዎችን ማስደሰት አለብኝ” የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል። ይህም የራሱን ፍላጎትና ስሜት ደብቆ ለሌሎች ይሁንታ ብቻ የሚኖር ስብዕና እንዲላበስ ሊያደርገዉ ይችላል።

ወደፊትም የፍቅር ሆነ የጓደኝነት ግንኙነት ሲመሰርት ሰዎችን ለማመን ይቸገራል። ሰዎች አንድ ቀን ጥለውኝ ይሄዳሉ የሚል ስጋት ስላለዉ ወይ ራሱን ቀድሞ ያገላል ካልሆነ ከመጠን በላይ ሰዎች ላይ ሊጣበቅ ይችላል። ታካሚዬ ላይ ያየሁትም ይሄንኑ ነበር።

ይህ ቀልድ መሳይ ጨዋታ በልጆች እያደገ ባለ ስነልቦና ላይ ከባድ አሻራ ይጥላልና መቅረት ያለበት ልማድ ነዉ።

#የአዕምሮ_ጤና_ግንዛቤ_ወር
#MentalHealthAwarenessMonth


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1