የADRA ኢትዮጵያ እና የኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የአረንጓዴ ኢነርጂ ፕሮጀክት በስኬት ተጠናቀቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | አድራ ኢትዮጵያ ከኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመሆን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገብረው የቆየውን የቪኪውኢፒ ወይም የግሪን ኢነርጂ ቲቪኢቲ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ መጠናቀቁን አስመልክቶም የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።

የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊው አቶ ሮቤል ጌታቸው በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ በአስተዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ130 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች አዲስና ተፈላጊ በሆነው የፀሐይ ብርሃን ኃይል ተከላና ጥገና ሙያ ላይ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረጉን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለሥልጠናው ዘርፍ ላበረከተው አቅም፣ በከተማና በገጠር ለፈጠረው የሥራ ዕድል እንዲሁም የአረንጓዴ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን በተግባር ለማሳየት ላከናወናቸው ተግባራት በቢሮውና በአስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኮሌጁ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ በበኩላቸው አድራ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎች የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ድሬዳዋን ተደራሽ ያደረገው በዚህ ፕሮጀክት መሆኑን አስታውሰዋል።

ተቋሙ በይፋዊ እንቅስቃሴዎችና በበርካታ በረከቶች ወደ ኮሌጁ የመጣ መሆኑንና በአረንጓዴ ኢነርጂ ላይ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሠሩ መንገድ የከፈተ ልዩ ፕሮጀክት እንደሆነም አክለዋል።

ዲኑ አክለውም ፕሮጀክቱ ያስቀመጠውን ግብ በማሳካት ረገድ መልካም አፈጻጸም እንደነበረው ጠቅሰው፣ የራሱ የጊዜ ገደብ ስላለው ዛሬ ማጠቃለያ ቢደረግም በቀጣይ በጋራ የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች በመኖራቸው ተቋማቸው ደስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የአድራ ኢትዮጵያ የፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን አዋኖ አድራ በ120 ሀገራት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው፣ ድርጅቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰው ተኮር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በውቢቷ ድሬዳዋ በነበረው የፕሮጀክት ሂደት የተመዘገበው ውጤት እጅግ የሚያኮራ መሆኑንና የአስተዳደሩን እንዲሁም የኮሌጁን አመራሮች ቁርጠኝነት የተመለከቱበት እንደነበረም አክለዋል።

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ በየነ ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ለባለድርሻ አካላት በዝርዝር አቅርበዋል።

በተጨማሪም በኮሌጁ የተጠናውና በፕሮጀክቱ ሂደት የመጣውን ለውጥ የሚገመግመው የምርምር ሰነድ ቀርቦ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ አመራሮች ከሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊው አቶ ሮቤል ጌታቸው እና ከኮሌጁ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ እጅ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የእውቅና ሰርተፊኬትና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

የአድራ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ዲማ ሳባ እንደገለጹት፣ ከጀርመን የልማት ትብብር ተቋም እና ከአድራ ጀርመን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር ከኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሲተገበር የነበረው ፕሮጀክት በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ ፍጻሜውን አግኝቷል።

#diredawa #greenenergy #tvet #adraethiopia #solarenergy #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: