የቡታጅራ ከተማ ገጽታና

- Advertisement -
Sidebar AD

የዐረፋ በዓል የትራንስፖርት ፈተናዎች

#Ethiopia | ስለ ቡታጅራ ከተማ ሲታሰብ በህይወት ባይኖርም በውብ ፅሁፎቹ ሁልጊዜም በልባችን የሚታወሰው ሀያሲ አብደላ እዝራ ወደ አእምሮ ይመጣል።

አብደላ ለስነ ፅሁፍ ስራው ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ተጉዞ በነበረበትና በሚወዳት ቡታጅራ ከተማ ነበር ህይወቱ ያለፈው።

ቡታጅራን በትዝታ ስቃኝ አብደላ ይህችን ከተማ ለስነ ፅሁፍ ስራ ምርጫዬ ናት ማለቱ ብቻ ሳይሆን ራሕማቶ የተባለውን የአእምሮ ህመምተኛ ሰው ከአሰፋ ጉያው ራሕማቶ የተሰኘ መጽሐፍና በአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ገጸባህሪ ጋር በማነጻጸር በአካል አግኝተን ለመስራት ያደረግነውን ጥረት አስታውሳለሁ።

አሟሟቱንና ህይወቱን በተመለከተ በወቅቱ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እሁድ ፕሮግራም ላይ ያዘጋጀውን የማስታወሻ ዝግጅትም አልረሳውም።

ከዚህ በተጨማሪ ስለ ቡታጅራ ሲነሳ መልካም ስብዕና ያላቸው የቡታጅራው ተወላጅ የናይጄሪያና የሴኔጋል ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ድንበሩ ዓለሙ ትዝ ይሉኛል። አምባሳደር ድንበሩን እንዲሁም የሸዋ ክፍለሀገር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ያደረገውን ስመ ጥሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በቀለ አየለና መምህር ተካልኝ አሳምረውን በመያዝ ከጋዜጠኛ በቀለ አመነና በርካታ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ዳይሬክተር ከሆነው ቢኒ ምዕራፍ ጋር በቡታጅራ የሰራነውን ፕሮግራም አስባለሁ።

ቡታጅራ በብዙ ትዝታዎች የተሞላች ከመሆኗም በላይ ዘርና ሃይማኖት ሳትለይ ሁሉንም በፍቅር የምትቀበል ከተማ በመሆኗ ሁልጊዜም በፍቅር አነሳታለሁ።

ይህ ስሜት በእኔ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዳለ አምናለሁ። ለጊዜው አስፈላጊ ስላልሆነ እንጂ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

የትናንቷ ቡታጅራ ብዙ የሚወራላት እንደነበረች ሁሉ የዛሬዋ ደግሞ ከትናንት ይልቅ ከፍ ብላ የዞን ዋና ከተማ በመሆን በየእለቱ በውበት እየጨመረችና በተቋማት ምስረታ እየገዘፈች ትገኛለች።

በተለይ በመጠናቀቅ ላይ ያለውና በፋውንቴኖች ዜማ የታጀበው የኮሪደር ልማት የሰጣት ውበት ለሰርጓ የተዘጋጀች ሙሽሪት አስመስሏታል።

የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶቿ፣ የምሽት መብራቷ እና በዚህ አመት ተማሪዎችን የተቀበለው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በሙሉ ትልቅ እመርታዎች ናቸው።

ስለ ከተማዋ ጽዳት ከተነሳ ደግሞ ያለማጋነን አብሯት የተወለደ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እኔ በግሌ በተደጋጋሚ በሄድኩ ቁጥር የቱቦዎችን ጽዳት ተመልክቼ በአዲስ ዘመንና በአዲስ አድማስ ጋዜጦች ላይ መጻፌን ማስታወስ እወዳለሁ።

ይህ ለቡታጅራ የማይለወጥ ድንቅ ክብሯ በመሆኑ እንዳይበላሽ አደራ እላለሁ።

ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ በጎነቷ የምናነሳት ቡታጅራ ከአንዳንድ ገጠመኞች በመነሳት ስሟ እንዳይጠለሽ የምሰጋበት ነገር አለ። ይህም በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዙሪያ የሚስተዋለው ዝርክርክነት ነው። በተለይ በየአመቱ በሚከበሩት የዐረፋና የመስቀል በዓላት ወደ ትውልድ ቀያቸው የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ሲጉላሉና ለዘራፊዎች ሲጋለጡ ማየት ልብ ይሰብራል። ይህ ችግር ዘወትር የሚታይ ቢሆንም በበዓላት ወቅት ግን የባሰና የተጋነነ ይሆናል።

አሁን በዐረፋ በዓል ዋዜማ ይህንን ማስታወስ ያስፈለገኝ ሰሞኑን በታዘብኩት ችግር ምክንያት ነው። በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ከየአቅጣጫው በቡታጅራ በኩል ወደ ወራቤና ሐሊቾ ይጓዛል። በዚህ መሃል ወደ አዲስ አበባ የሚሄድም አለ።

ነገር ግን ተሳፋሪዎች ወደ መናኸሪያ ከመግባታቸው በፊት እስከ በሩ ድረስ በመከተል፣ በማባበል፣ በመጎተትና በማደናገር በየጥሻው ስር ወደተደበቁ መኪኖች የሚወስዱ የደላሎች ቁጥር በርካታ ነው። ይህ ተሳፋሪዎችን የማዋከብ ስራ ሰዎችን ለዘረፋና ለአደጋ ያጋልጣል።

ከተሳፋሪዎች እንደሰማሁት በህገወጥ መንገድ ከውጭ የሚጫኑ ሰዎች ያለ ምንም የህግ ከለላ ከታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ መኪና ሲጎተቱ ንብረታቸውን ይዘረፋሉ።

በአይኔ እንደታዘብኩት በዚህች ውብና አዳጊ ከተማ ይህንን ወቅታዊ አደጋ የሚከላከል አንድም የህግ አስከባሪ ጣልቃ ሲገባ አልታየም። ጥያቄዬ በአንዲት የዞን ዋና ከተማ በርካታ እንግዶች ሊስተናገዱ ሲመጡ ለምን በቂ ዝግጅት አይደረግም?

እንዲህ ያለው ዝርክርክነት የከተማዋን ገጽታ እንደሚያበላሽ ለምን አልታሰበም? አሁንም ቢሆን አልረፈደምና እስከ በዓሉ ቀንና መመለሻ ድረስ ህዝቡ በነጣቂዎች እንዳይዘረፍ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ የኃላፊዎች ግዴታ ነው።

የቡታጅራ ከተማ ውበት ሁለንተናዊ እንዲሆን በመናኸሪያ ውስጥ ያለውን የማጉላላት ችግር፣ የቲኬት መቁረጫ ቴሌብርና የባንክ አገልግሎት አለመስጠትን ጨምሮ መፍታት እንዲሁም ከመናኸሪያ ውጭ ያለውን የህገወጦች ወከባና ዘረፋ ማስቆም እንደሚገባ ማሳሰብ ያስፈልጋል።

ደረጀ በላይነህ

#ቡታጅራ #የአረፋበዓል #በትራንስፖርት #የኮሪደርልማት #የህዝብጉልላት #የደላሎችወከባ #የዞንከተማ #ኢትዮጵያ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2