#Ethiopia | አፍሪካውያን በራሳቸው ጥረትና አቅም እየገነቧት ያለችውን አህጉር ለዓለም ለማስተዋወቅና ስኬቶቻቸውን ወደ አደባባይ ለማውጣት ያለመ #NotWaiting (አልጠብቅም) ዘመቻ ተጀመረ።
ይህ አህጉር አቀፍ ዘመቻ ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም (May 25, 2026) በአፍሪካ ቀን በይፋ መጀመሩ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ፣ ጆሃንስበርግ፣ ናይሮቢ፣ ሌጎስ እና አክራ ከተሞች በጋራ ይፋ የተደረገው ይህ ዘመቻ፤ «ኦፖርቹኒቲ አፍሪካ» (Opportunity Africa) በተሰኘ ተቋም የሚመራ ነው።
በአህጉሪቱና በዲያስፖራው የሚገኙ አፍሪካውያን በአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ እያመጡት ያለውን በጎ ተጽዕኖ፣ አዳዲስ ዕይታዎችና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የዘመቻው ዋነኛ መርህ አፍሪካውያን ስለ ራሳቸው ያላቸውን አመለካከት ሲቀይሩ፣ ቀሪው ዓለምም ስለ አፍሪካ ያለውን ዕይታ ይቀይራል በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው።
በአሁኑ ወቅት በርካታ አፍሪካውያን ሥራ ፈጣሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን እየገነቡና ማኅበረሰባቸውን እየለወጡ ቢሆንም፣ እነዚህ የስኬት ታሪኮች አሁንም ድረስ በችግር፣ በረሃብና በውስንነቶች ላይ ብቻ በሚያተኩሩ አሉታዊ ትረካዎች (narratives) እየተሸፈኑ መሆኑ ተጠቅሷል።
የዚህ እንቅስቃሴ ዓላማ አፍሪካን በተመለከተ የሚነገሩ ትረካዎችን ሚዛን ለመጠበቅና ፍሬያማ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን፣ ግንባታዎችንና እድገቶችን በጋራ ድምፅ ከፍ አድርጎ ለማሳየት ነው።
ይህ እንቅስቃሴ የጥቂት ስኬታማ ሰዎች ታሪክ ሳይሆን፣ መላው አህጉሪቱ እያሳየችው ያለውን የእድገት ጉዞና አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይ መሆኑ ተመልክቷል።
አዘጋጆቹ መላው የአፍሪካ ሕዝብና ትውልደ አፍሪካውያን በፈጠራ ሥራዎቻቸው፣ ስኬቶቻቸውና አዳዲስ ሐሳቦቻቸው ላይ ያተኮሩ ታሪኮችን በ#NotWaiting የሃሽታግ ምልክት በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲያጋሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ፍላጎት ያላቸው ወገኖች www.notwaiting.africa በተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ በመግባት የዘመቻውን ማኒፌስቶ መፈረም እንደሚችሉ ተገልጿል።
ይህ ዘመቻ ዛሬ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፣ በየወሩ በ25ኛው ቀን እየታደሰ የሚቀጥልና አፍሪካውያን በአንድነት በመሆን የኢንተርኔት ዓለምን በስኬት፣ በፈጠራና በዕድሎች ታሪክ የሚያጥለቀልቁበት ተከታታይ መድረክ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.