#Ethiopia | አቶ ካሳ በ92 ዓመት እድሜያቸው ይኖሩበት በነበረው አሜሪካ ሀገር ህይወታቸው ያለፈው በዛሬው እለት ነው።
ኢንጂነር ካሳ ገብሬ ከኢትዮጵያ ህንፃ ኮሌጅ በሲቪል ምህንድስና ካናዳ ሀገር በሚገኘው የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአንድ ዓመት የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
በትምህርት ሚኒስቴር በዋና መሃንዲስነት፣ በቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትርነት፣ በኤርትራ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና መሃንዲስ፣ በሕንጻ ኮንስትራክሽን ሚኒስትርነት እና በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች እስከ ደርግ ስርዓት ማብቃት ድርስ አገልግለዋል።
ኢንጂነር ካሳ በደርግ ስርዓት ወቅት የተሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችንም መርተዋል።
በሶማሌ ወረራ ጦርነት ወቅት ህዝባዊ ሠራዊት የሰለጠንበትን የታጠቅ ጦር ሜዳ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዘጋጀታቸው ከሚጠቀስላቸው ስራዎቻቸው መከከል ይገኝበታል።
የጀግኖችና ህፃናት አምባ ምስረታዎች ወቅት የግንባታ ዘርፉን መርተዋል።
የጣና በለስ ግድብ፣ የቀይ መስቀል ሕንጻ፣ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ ፍልውሃ ሕንጻዎች፣ አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን፣ በርካታ የከተማ ፕላኖችና ድልድዮች ከታላላቅ ሥራዎቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
በዚህም ጉልህ አስተዋጿቸው ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ከመሠረት ጣዮች መካከል አንዱ ተደርገውም ይነሳሉ።
አገሪቷ ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ውስጥ በገባችበት ወቅትም ዜጎችን ድርቅ ካለበት ወደ ድርቅ ወደሌለበት አካባቢ በማዛወር ከእልቂትና ከረሃብ አደጋ በመታደግ ትልቅ ሰብዓዊ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውምን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ኢንጂነር ካሳ በኢህአዴግ መንግሥት ዘመን 12 ዓመት ከ3 ወር ታስረዋል።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ አብዛኛውን ኑሯቸውን ያደረጉት በአሜሪካ ሀገር ሲሆን መጽሐፍ ጽፈው አጠናቅቀው፣ ግን ለሕትመት ሳይበቃ አረፈዋል።
አቶ ካሳ ገብሬ የሁለት ወንዶች እና የሁለት ሴቶች ልጆች አባትም ነበሩ።
በ92 ዓመት እድሜያቸው ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኢንጂነር ካሳ ገብሬ የቀብር ስነስርዓታቸው በአሜሪካን ሀገር ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል፣ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም፣ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ በ3:30 ሰዓት የሚፈፀም ሲሆን በአዲስ አበባ የመታሰቢያ መርሃግብር በቀጣይ ቀናት ይደረግላቸዋል ተብሏል።
ዘገባው የሸገር ኤፍ ኤም ነው
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.