ጤና ሚኒስቴር ከጣሊያን ሀገር የመጡ በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች ላከናወኑት የሕፃናት ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና ምስጋናና ዕውቅና ሰጠ

- Advertisement -
Sidebar AD

የጤና ሚኒስቴር በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ አማካይነት ከጣልያን ሀገር የመጡ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች፣ ከኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት 80 የልብ ሕሙማን ሕፃናት በሁለት ጊዜ ምልልስ
በ15 ቀናት ጊዜያት ውስጥ የነጻ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት
በመስጠታቸው የምስጋናና የእውቅና ሠርተፊኬት ሰጠ።

ትላንት ግንቦት 18/2018 ዓ.ም በአራዳ ፓርክ በተከናወነው መርሐግብር ባለሙያዎቹ አገልግሎቱን የሰጡት በሁለት ዙር ተልእኮ መኾኑ የተጠቀሰ ሲሆን 48 ሕፃናት በአዲስ አበባ ኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል፣ 9 ሕፃናት በጂግጂጋ እንዲሁም 23 ሕፃናት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል (በጎንደር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ) የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾናቸው ተነግሯል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ለተሰጠው አገልግሎት በጤና ሚኒስቴር፣ በራሳቸው ስምና ከሁሉም በላይ በዚህ ሕክምና ተጠቃሚ በሆነው ማህበረሰብ ስም ላቅ ያለ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ይህ መልካም ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል። በቀጣይም ለሚከናወኑ መሰል ተግባራት ጤና ሚኒስቴርም አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ለዚህ ዓላማ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በተለይም ለኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ በገንዘብ እና በቴክኒክ ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግከሎት በ45 ቀናት ለ175 ሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት በጤና ሚኒስቴር፣ በኸርት ቱ ኸርት ችልድረንስ ኤይድ እና በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት መካከል የተደረገ ስምምነት አካል ነው።

አቶ ብርሃን ተድላ የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ በበኩላቸው የጤና ሚኒስቴር የተከናወነውን የበጎ ተግባር ትልቅ ዋጋ መስጠቱ ሌሎችም ተመሳሳይ ተልእኮዎች በአርአያነት የሚታይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኽርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ በገባው ቃል መሰረት ስራዎቹ በአጭር ጊዜያት እንደሚያጠናቅቅም አቶ ብርሃን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ለስራው የስምምነቱ አካል የኾኑ የመንግስት፣ የግል ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መኾኑን በማስታወስ የስራው አጠቃላይ ሪፖርት እኤአ ጁን 10 ከተጠናቀቀ በኋላ ሌላ የምስጋና መርሐግብር እንደሚኖር ዶ/ር አስቻለው ወርቁ የጤና ሚኒስቴር አማካሪ አረጋግጠዋል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1