#Ethiopia | በኢትዮጵያ የማርሻል አርት ስፖርትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመው እና በ9 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የሽልማት በጀት የተዘጋጀው የአድዋ ፋይት ናይት የውድድር ምሽት የፊታችን ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ይካሄዳል።
ይህ ታላቅ ስፖርታዊ ሁነት የድብልቅ ማርሻል አርት (MMA)፣ የቦክስ እና የሙአይ ታይ ፍልሚያዎችን በአንድ መድረክ ላይ በማስተናገድ በአይነቱ ልዩና ድምቅ ያለ ዝግጅት እንደሚሆን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
በዕለቱ ከሚጠበቁት ዋና ዋና ፍልሚያዎች መካከል የቀድሞው ሻምፒዮን ዮሐንስ ስለሺ (ጆኒ) ከሴዶ ማርሻል አርት (ካሚል) ጋር በ85 ኪሎግራም የሚያደርጉት የኤምኤምኤ ፍልሚያ ቀዳሚውና ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነው።
በሁለተኛው ዋና የቦክስ ፍልሚያ ላይ ድንቅ ስነ ምግባር ያለው መስፍን ብሩ በ71 ኪሎግራም የዋባ ቤልት ባለቤት ከሆነውና ከኡጋንዳ ከሚመጣው ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪ ጋር ለ6 ዙር የሚቆይ ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋል።
ሦስተኛው ዋና ፍልሚያ የሙአይ ታይ የክብር ቀበቶን የሚያስረክብ ሲሆን፣ ረቢቅ ሳኒ የታንዛኒያን ተወዳዳሪ አሸንፎ የመጣውንና የ2025 የአለም የሙአይ ታይ ሻምፒዮን የሆነውን ሱዳናዊውን ጀምስ ማጆክን የሚገጥምበት በመሆኑ ለስፖርቱ አፍቃሪያን ልዩ አጋጣሚን ይፈጥራል።
ከእነዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ተመርጠው የተዘጋጁ አራት የቦክስ ጨዋታዎች በዕለቱ ይካሄዳሉ።
በዚህም መሰረት በ60 ኪሎግራም ሃይማኖት ደሳለኝ (ታይሰን) ከአብርሃም አለም ጋር፣ በ54 ኪሎግራም ደሳለኝ ሲሳይ ከሱራፌል አላዩ ጋር፣ እንዲሁም በ48 ኪሎግራም እሱባለው ሞላ ከቢኒያም በሪሁ ጋር የሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች በቦክስ ካርዱ ላይ ተካተዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ኢንተግሬትድ ማርሻል አርት በሚዘጋጀው የኖክአውት ቶርናመንት አሸናፊ የሚሆኑት ስፖርተኞች እንደየምድባቸው ተለይተው ለእድሪስ እና ለሀብታሙ የሙአይ ታይ ተጋጣሚ ሆነው እንዲቀርቡ ይደረጋል።
በተጨማሪም ባለፈው ዝግጅት የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከልና የሴቶችን ተሳትፎ ለማበረታታት የሴቶች የሙአይ ታይ ውድድር የተካተተ ሲሆን፣ በታይላንድ ሀገሯን ወክላ ድንቅ ድል ያስመዘገበችው ዘሃራ ከኢንተግሬትድ ማርሻል አርት በሚመረጥላት ሴት ተፋላሚ ጋር የምትገጥም ይሆናል።
በአጠቃላይ 10 ያህል ትልልቅ ፍልሚያዎችን የያዘውና በአድዋ ስም የተሰየመው የውድድር ምሽት የተመልካቾችን መጉላላት ለመቀነስ የዲጂታል ቲኬት ሽያጭና የተቁጠረ የወንበር ቁጥር አሰራርን እንደሚከተል አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በዕለቱ ለሚካሄዱት ውድድሮች የሚሰጠው የዳኝነትና የነጥብ አቆጣጠር ሙሉ በሙሉ በቦክስና በኢንተግሬትድ ማርሻል አርት ፌዴሬሽኖች ሙያዊ ኃላፊነት የሚመራ ሲሆን፣ የተዘጋጀው የ9 ሚሊዮን ብር የሽልማት ገንዘብም እንደየውድድሩ አይነት ለአሸናፊዎቹ ተከፋፍሎ ይሰጣል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዝርዝር ዝግጅቶችን የተመለከተ የጋራ መግባቢያ ስምምነት በኢትዮጵያ ፌንቲንግና ኮምባት ስፖርት (ETFC)፣ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንዲሁም በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መካከል ተፈርሟል።
#የአድዋፋይትናይት #ማርሻልአርት #ቦክስ #ሙአይታይ #የአድዋመታሰቢያ #ስፖርት #ኢትዮጵያ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen









No comments yet.