#Fastmereja I በከተማዋ በተካሄደው የኮሪደር ልማት ምክንያት ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረው ህንጻ እንዲፈርስ የተደረገው የልዩ ህክምና ክሊኒክ፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎቹን ይበልጥ በማዘመን እና አቅሙን በማሳደግ በአዲስ መልክ በዛሬዉ እለት አስመርቆ ስራ አስጀምሯል።
ክሊኒኩ አሁን ላይ አገልግሎቱን በስፋት መቀጠል የጀመረው በየካ ክፍለ ከተማ፣ ታቦት ማደሪያ እግር ኳስ ሜዳ አጠገብ በሚገኘውና አዲስ በገነባው ባለ 22 ክፍል ዘመናዊ ህንጻ ላይ መሆኑ ታውቋል።
የተቋሙ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ዳዊት አማረ በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር በይዘቱም ሆነ በህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እራሱን በከፍተኛ ደረጃ ማዘመኑን ገልፀዋል።
ክሊኒኩ በተለይም በውስጥ ደዌ እና በሳንባ ስፔሻሊስት (Pulmonology) የህክምና ዘርፍ ላይ ያተኮረ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ለድንገተኛ አደጋዎችና ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ፈላጊዎችም ቀልጣፋ አገልግሎት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
“ጤና የእያንዳንዱ ሰው መሰረታዊ መብት ነው” የሚል ፅኑ እምነት አለን ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ታካሚዎችን በታማኝነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውንና አሁንም ማህበረሰቡን በተሻለ ጥራትና ምቾት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዲሱ ህንፃ የህክምና ተቋም ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ፣ ህፃናትን ጨምሮ ማንኛውንም ታካሚ በተገቢው ሁኔታ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎችንና ዘመናዊ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ማሟላቱ ተገልጿል።
ተቋሙ በኮሪደር ልማት ምክንያት ቢፈርስም፣ ላለፉት 14 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥበት በነበረው በዚሁ አካባቢ ለታካሚዎች የትራንስፖርት ምቾትን ታሳቢ ባደረገ ስፍራ ላይ በላቀ የህክምና መሳሪያና አደረጃጀት ስራ መጀመሩ ተገልጿል።
ክሊኒኩ ለ56 የህክምና ባለሙያዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ወደ 23 የሚሆኑ ስፔሻሊስት እና ሰብ-ስፔሻሊስት ዶክተሮች በተቋሙ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ነዉ የተገለፀዉ።
በዕለቱም ክሊኒኩ ባለፉት ዓመታት አብረዋቸው ለቆሙ፣ እምነት ለጣሉባቸው ታካሚዎች እና በአስቸጋሪ ወቅቶች ስራው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ድጋፍ ላደረጉ ባልደረቦች ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል።



Source: FastMereja









No comments yet.