የአርሰናል የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ህልም በፍጹም ቅጣት ምት መክሸፍ እና አጨቃጫቂው የምሽቱ ጨዋታ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በለንደን የሚገኙት አለባቸው ደሳለኝ አበሻ እንደዘገቡት የፒኤስጂ እና የአርሰናል የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ፍልሚያ በዳኝነት ውሳኔዎች ታጅቦ እጅግ አነጋጋሪ በሆነ መልኩ ተጠናቋል።

በውድድር ዘመኑ በሻምፒዮንስ ሊጉ ምንም ሳይሸነፍ ለፍጻሜ የደረሰው አርሰናል መደበኛውና ተጨማሪው ሰዓት 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ በተሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት 4 ለ 3 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል። ይህ ምሽት ለአርሰናል ደጋፊዎች እጅግ ልብ ሰባሪ ነበር።

ስለ ጨዋታው የስፖርት ተንታኞችና ጋዜጠኞች የሰጧቸውን ዋና ዋና አስተያየቶች ከመመልከታችን በፊት የጨዋታውን አጠቃላይ ገጽታ በወፍ በረር እንቃኝ።

የአርሰናል የመከላከል ጥበብ እና የኮከቦች መዛል
ጨዋታው ከተጀመረበት ደቂቃ አንስቶ እስከ ፍጹም ቅጣት ምት ድረስ የአርሰናል የመከላከል ብቃት ፍጹም ሊደነቅ የሚገባው ነበር። ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዘመን እንደፈለገ ጎል እያዘነበ የመጣ ፈጣንና ጠንካራ የፊት መስመር ጥቃት ያለው ክለብ መሆኑ ይታወቃል።

አርሰናል ግን እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በከፍተኛ ዲሲፕሊን ተቆልፎ የፒኤስጂን አስፈሪ የማጥቃት ኃይል አምክኖ የዋለበት መንገድ ቡድኑ ምን ያህል ጠንካራ መዋቅር እንዳለው ያሳየበት ምሽት ነበር። ነገር ግን የኳስ ጨካኝነት እዚህ ላይ ነው 120 ደቂቃ ሙሉ በጥንካሬ ተከላክለህ በመጨረሻው የዕድል ፈተና በፍጹም ቅጣት ምት ዋንጫውን ማጣት በእውነትም ያማል።

በርካታ ተንታኞች በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የአሰላለፍ ውሳኔ ላይ ትኩረት አድርገዋል። በተለይም ቶማስ ፓርቴይን ወይም የተለመዱ ተከላካዮችን ከመጠቀም ይልቅ ክሪስቲያን ሞስኬራን በቀኝ ተከላካይነት መሰለፉ ስህተት እንደነበር አንስተው ተችተዋል። ፒኤስጂ በሁለተኛው አጋማሽ በክቪቻ ኳራፅኬሊያ በኩል ጫና ሲፈጥር ሞስኬራ ፍጹም ቅጣት ምት የተሰጠበትን ጥፋት በመስራቱ የጨዋታውን አቅጣጫ ቀይሮታል ብለዋል።

አርሰናል ጨዋታውን በካይ ሀቨርትዝ ቀደመ ግብ ድንቅ አጀማመር ቢያደርግም በሁለተኛው አጋማሽ እና በትርፍ ሰዓት ላይ ቡድኑ በከፍተኛ ሁኔታ መዛሉ ታይቷል። ፒኤስጂ 72 በመቶ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበረው ሲሆን አርሰናል ሙሉ ጨዋታውን በመከላከል ማሳለፉ ለፍጹም ቅጣት ምት ሲደርሱ ተጫዋቾቹ ላይ የትኩረት ማጣት እንዲከሰትና የአርሰናል አስደናቂ ጥንካሬ እንዲዝል አድርጎታል።

የዳኝነት ውሳኔዎች እና የቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) ውዝግብ
የዳኝነት ውሳኔው በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም በኤክስ እና በፌስቡክ ላይ በደጋፊዎችና በስፖርት ተንታኞች መካከል እጅግ ሞቅ ያለና የአርሰናልን ደጋፊዎች ያስቆጣ አጀንዳ ሆኗል። ዳኛው አድላዊ ነበሩ በሚል ማህበራዊ ሚዲያውን እያነጋገሩ ያሉት 3 ዋና ዋና አጨቃጫቂ ውሳኔዎች የሚከተሉት ናቸው።

በኖኒ ማዱዌኬ ላይ የተፈጸመው ጥፋት እና የቪዲዮ ረዳት ዳኛ ዝምታ ጉዳይ በትክክል ፍጹም ቅጣት ምት መሆን ነበረበት ተብሏል። የፒኤስጂው ተከላካይ ኑኖ ሜንዴስ በሳጥን ውስጥ ማዱዌኬን በግልጽ ሲገፋውና ሲያንገላታው ቢታይም የቪዲዮ ረዳት ዳኛው ዋናውን ዳኛ ሄዶ በስክሪን እንኳ እንዲያይ አለመጋበዙ ግልጽ አድሎ ነው በሚል የአርሰናል ደጋፊዎች ቁጣቸውን እየገለፁ ይገኛሉ። ገለልተኛ ተንታኞችም የግፊው ኃይል ለፍጹም ቅጣት ምት በቂ ባይሆን እንኳ ጉዳዩ ቢያንስ በቪዲዮ ረዳት ዳኛ መታየት እንደነበረበት ይስማማሉ።

የእርምጃዎች ድርብ መስፈርት በሁለተኛው አጋማሽ ክሪስቲያን ሞስኬራ በክቪቻ ኳራፅኬሊያ ላይ በሰራው ጥፋት ፒኤስጂ በቀላሉ የፍጹም ቅጣት ምት አግኝቷል። ብዙዎች ኳራፅኬሊያ በቀላሉ ነው የወደቀው ዳኛው ግን ለፒኤስጂ የነበራቸው አዝማሚያ ለስላሳ ስለነበር ወዲያውኑ ፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ በማለት ይተቻሉ። በተመሳሳይ ጥፋት በአርሰናል በኩል የቀረቡት ጥያቄዎች ውድቅ መደረጋቸው የዳኛውን ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል።

የሰዓት ማጥፋት እርምጃዎች መዘግየትን በተመለከተ የፒኤስጂ ተጫዋቾች ሆን ብለው ሰዓት ሲያጠፉ እና ጨዋታውን ሲያደናቅፉ ዳኛው ጥብቅ እርምጃ አለመውሰዳቸው ሌላው ቅሬታ ነው። በተቃራኒው በአርሰናል ተጫዋቾች ላይ የተሰጡት የቅጣት ውሳኔዎች ፍጹም ጥብቅ እና ቡድኑን የተጫኑ ነበሩ ተብሏል።

የአርሰናል የቀድሞ ኮከብ አለን ስሚዝ ጨምሮ በርካታ ተንታኞች እንደሚስማሙት ዳኛው በጨዋታው ላይ የተጠቀሙት ድርብ መስፈርት አርሰናል ዋንጫውን እንዲያጣ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል።
የስፖርት ተንታኞች እንደሚሉት የፍጹም ቅጣት ምት ሁሌም የዕድል ጉዳይ ነው።

በጨዋታው ላይ ኤበሬቺ ኤዜ ሳይጠቀምበት የቀረውን ኳስ ዴቪድ ራያ የኑኖ ሜንዴስን መቅጫ ምት በማዳን ተስፋ ቢመልስም በመጨረሻው ወሳኝ ምት ተከላካዩ ጋብሬል ማጋልሃሽ ኳሱን ወደ ላይ መስቀሉ ጨካኝ የሆነ የውጤት መደምደሚያ ነበር። ሆኖም ጋብሬል በጨዋታው ላይ የነበረው ድንቅ የመከላከል ብቃት ሳይዘነጋ ይህ ስህተት እሱን ብቻ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደማይገባ ተንታኞች ይሟገታሉ።

የሳካ እና ኦዴጋርድ መቀየር ስህተት ነበር?

ሚኬል አርቴታ ቡካዮ ሳካንና ማርቲን ኦዴጋርድን በማስወጣቱ ለሽንፈቱ ምክንያት ሆኗል ለሚለው ጥያቄ ተንታኞች ሁለት ዋና ዋና እይታዎችን እያነሱ ነው።

በአንድ በኩል ሳካ እና ኦዴጋርድ የቡድኑ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በፍጹም ቅጣት ምት ወቅት እጅግ አስተማማኝ የተረጋጉና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው። እነሱ በሌሉበት ሜዳ ላይ የቀሩት ወጣት ወይም የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች እንደ ጋብሬል ማጋልሃሽ የፍጹም ቅጣት ምት የመምታት ከባድ ጫና እንዲወድቅባቸው አድርጓል። በተጨማሪም ሁለቱ ኮከቦች ሲወጡ አርሰናል ኳስን መስርቶ ማጥቃትና ፒኤስጂን ወደ ኋላ ማስጨነቅ ሙሉ በሙሉ አቆመ።

ይህም ፒኤስጂዎች ያለ ምንም ስጋት ሙሉ ኃይላቸውን ወደ አርሰናል ሳጥን እንዲልኩና በአርሰናል ተከላካዮች ላይ ከፍተኛ የአእምሮና የሰውነት ድካም እንዲፈጠር አድርጓል ይላሉ።

በሌላ በኩል ጨዋታው ወደ ትርፍ ሰዓት ሲያመራ ሳካ እና ኦዴጋርድ በፒኤስጂ ተጫዋቾች ከፍተኛ ክትትልና ጫና ስለነበረባቸው በከፍተኛ ሁኔታ ዝለው ነበር።

አርቴታ እነሱን የቀየረው የጡንቻ ጉዳት እንዳይገጥማቸውና ትኩስ ጉልበት ያላቸውን ተጫዋቾች ለምሳሌ ማዱዌኬን በማስገባት የፒኤስጂን መስመር ለመስበር በማሰብ ሊሆን ይችላል የሚሉም አሉ።

ሆኖም አርቴታ ጨዋታውን በ120 ደቂቃ ውስጥ ለመጨረስ ወይም በመከላከል ለመጨረስ አስቦ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ጨዋታው ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ማምራቱ የማይቀር መሆኑን እያወቀ ሁለቱን ምርጥ የቅጣት ምት መቺዎቹን እና የቡድኑን የልብ ትርታዎች ቀይሮ ማስወጣቱ በታክቲክ ደረጃ ትልቅ ስህተት እንደነበር ይነገራል።

ይህ የሻምፒዮንስ ሊግ ሽንፈት ለአርሰናል እና ለደጋፊዎቹ እጅግ መራራ ምሽት ቢሆንም ክለቡ በዚህ የውድድር ዘመን የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳቱ ትልቅ ስኬት ማስመዝገቡ አይዘነጋም።

ቡድኑ ካሳየው አስደናቂ ጥንካሬ እና መዋቅር አንፃር በቀጣይ ዓመታት ይበልጥ ጠንክሮ እና ተምሮበት እንደሚመለስ የስፖርት ተንታኞች ትልቅ ተስፋ ጥለውበታል።

አለባቸው ደሳለኝ ለንደን 🇬🇧

#arsenal #psg #championsleague #football #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1