የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን የቅድመ ምርጫ ትዝብትና የሴቶች ተሳትፎ ሪፖርት ይፋ አደረገ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ሲያከናውን የቆየውን ሰፊ የቅድመ ምርጫ ትዝብትና የሴቶች ተሳትፎ የዳሰሰበትን አጠቃላይ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ፌዴሬሽኑ እንደገለጸው፣ በምርጫው ሂደት የሴቶች መራጭነት ተሳትፎ ከፍተኛ ታሪካዊ ውጤት የታየበት ቢሆንም፣ በዕጩነት የመቅረብ እና የመወዳደር ምጣኔያቸው ግን አሁንም ሰፊ ክፍተት ያለበትና ትኩረት የሚሻ መሆኑን አመልክቷል።

​በዚሁ ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት፣ በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገቡት 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 አጠቃላይ መራጮች ውስጥ 26 ሚሊዮን 667 ሺህ 132 ማለትም 49.3 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ታውቋል ።

ይህ ከፍተኛ የመራጭነት ቁጥር የታየ ቢሆንም፣ በዕጩነት ደረጃ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡት ሴቶች ግን 23.1 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፣ ለአጠቃላይ ብሔራዊ ምክር ቤት ደግሞ የሴቶች ዕጩዎች ድርሻ 25.8 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ አኃዝ በሴቶች መራጭነትና ዕጩነት መካከል የ23.5 በመቶ ሰፊ የአሳታፊነት ልዩነት ወይም ክፍተት መኖሩን በግልጽ እንደሚያሳይ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

​የሴቶች ፌዴሬሽን የዜጎችን ንቃተ ህሊና ለማሳደግና መራጮችን ለማስተማር ሰፊ የቴክኖሎጂና የሚዲያ ዘመቻዎችን ማካሄዱን በዝርዝር አስረድቷል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ ስምምነት 255 ሚሊዮን የፅሁፍ መልዕክቶች በነፃ የተላኩ ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ6 ቋንቋዎች የተዘጋጁ መልዕክቶች 42 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሴቶችና 87 ሚሊዮን ለሚሆኑ አጠቃላይ ተመዝጋቢዎች መድረስ መቻላቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በኤፍ ኤም ሬዲዮና በቴሌግራም ቦት አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የምርጫ ትምህርት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ባልተደጋገመ ስሌት ከ90 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዘመቻውን መድረስ መቻሉ ተረጋግጧል።

​ሂደቱን በታዛቢነት ከመከታተል አንፃርም ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉንና 5 ሺህ 432 ታዛቢዎችን ለማሰማራት አቅዶ እንደነበር አስታውቋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ 267 የረጅም ጊዜ ታዛቢ አሰልጣኞች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ እነዚህ አሰልጣኞች በተራቸው 5 ሺህ 165 የሚሆኑ የአጭር ጊዜ ታዛቢዎችን በየደረጃው ማሰልጠን መቻላቸው በስራ አፈፃፀሙ ላይ ተገልጿል።

​በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ለቀጣይ ምርጫዎች መሻሻል የሚረዱ በርካታ የውሳኔ ሐሳቦችንና ምክረ ሐሳቦችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች አቅርቧል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱን ይበልጥ እንዲያሻሽልና የታዛቢዎችን የገንዘብና የዕቃዎች አቅርቦት በወቅቱ እንዲያደርስ የጠየቀው ፌዴሬሽኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢያንስ 30 በመቶ የሴቶች ዕጩ ተሳትፎን የሚያረጋግጥ ውስጣዊ ደንብ እንዲያወጡና የሴቶችን በራስ የመተማመን አቅም የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በፅኑ አሳስቧል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: