#Ethiopia | በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች በስፋት የሚታወቀው አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የአርቲስቱ የቀብር ስነ ስርዓት ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአማኑኤል ቤተክርስቲያን ከቀኑ 6:00 ሰዓት ይፈጸማል።
ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በሙያ ህይወቱ በታማኝነት ባገለገለበት ታሪካዊው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሽኝት እና የሻማ ማብራት መርሃ ግብር ይከናወናል።
***
የሁለገቡ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው አጭር የህይወት ታሪክ
የመድረኩ እንዝርት ሁለገቡ የጥበብ ሰው አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከእናቱ ከወ/ሮ ብዙነሽ ጓንጉል እና ከአባቱ ከአቶ ምስጋናው ደርኬሮ ሰኔ 15/ 1958 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አማኑኤል አጂፕ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ተወለደ፡፡ ለአቅመ ፊደል ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በደጃዝማች ኃይሉ ተስፋዬ ትምህርት ቤት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ ትምሀርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተምሮ አጠናቋል።
ከውዝዋዜ ጋር ገና ተማሪ እያለ የተወዳጀው ሁለገቡ ከያኒ ኪዳኔ ምስጋናው የጥበብ ጉዞውን በቀበሌ ኪነትና በከፍተኛ ኪነት ውስጥ አድርጎ መዳረሻውን በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በማድረግ በ1977 ዓ.ም በውዝዋዜ ሙያ ለመቀጠር በቅቷል፡፡ የአርቲስት ኪዳኔ የሙያ ፍቅር፣ ችሎታና ስነምግባር ያስደመማቸው የውዝዋዜ ክፍል አሰልጣኞችና ኃላፊዎች ከተወዛዋዥነት ወደ ረዳት አሰልጣኝነት እንዲያድግ በማድረጋቸው ከ1983-1990 ዓ.ም ድረስ በረዳት አሰልጣኝነት ሙያ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ጥበበኛው ኪዳኒ በረዳትነት የጀመረውን የአሰልጣኝነት ስራውን ከፍ በማድረግ ከ1991 እሰከ 1992 በቋሚ አሰልጣኝነት ተመድቦ በርካታ ባለሙያዎችን በክህሎት፣ በስነምግባርና በጥበብ አሰልጥኖ ለውዝዋዜ ሙያ መስፋፋትና አድገት የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል፡፡
በውዝዋዜ ጥበብ በማለዳው የተነደፈው ኪዳኔ በእውቀት፣ በልምድና በፈጠራ እየጎመራና አንቱታን እያተረፈ ሲመጣ አድማሱን በማስፋት በአንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተዛውሮ ከ1992 እሰከ 2007 ዓ.ም በዋና አሰልጣኝነትና በኬሮጋራፈርነት በርካታ በሀገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ግዘፍ የነሱ መድረኮች ላይ የቀረቡ የውዝዋዜ ስራዎችን በማዘጋጀት፣ በማማከርና በመምራት ከሰው ልብና አእምሮ የማይጠፉ ደማቅ ኪነጥበባዊ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
አርቲስት ኪዳኔ ፈጣን የፈጠራ፣ የማደራጀትና የመምራት አቅም የነበረው ብርቱ የጥበብ ሰው ነበር፡፡ በርካታ ተወዛዋዦች የሚገኙበት የጥበብ መድረክ ካለ እዛ የጥበብ መድረክ ላይ ኪዳኔ መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ህልም ነበር፡፡ የኪዳኔ የፈጠራ፣ የውዝዋዜ ችሎታና የውዝዋዜ ዝግጅት ጥበብ የታየባቸው አያሌ የውዝዋዜ ጥበብ ስራዎች ህያው መስክሮቹ ናቸው፡፡ በፋሽስት ጣሊያን የተዘረፈው የአክሱም ሀውልት ወደ ሀገሩ ሲመለስ ለነበረው አቀባበል በተዘጋጀው የኪነጥበብ መድረክ ላይ በአዲስ አበባና በአክሱም ከተማ ግዙፍ የውዝዋዜ ዝግጅት፣ በህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ በተዘጋጀው የጥበብ መድረክ፣ በሚሊኒዬም አዳራሽ፣ በባህዳር ጣና ሐይቅ ላይ የውዝዋዜ የጀልባ ላይ ትርኢት፣ የአዲስ ዓመት የበዓል ዝግጅቶች ላይ ጥበብ፣ ባህል፣ ፈጠራና ውበት የተመላባቸው በርካታ ተወዛዋዦች የተሳተፉባቸውን የጥበብ ስራዎች በማዘጋጀት የጥበብና የሀገር ባለውለታነቱን አስመስክሯል፡፡
በአንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከአስራ አምስት ዓመት በላይ በአሰልጣኝነት ሲሰራ ከቆየ በኋላ ከ2007 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ወደ ቀድሞ የሙያ ቤቱ የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አደራሽ ተዛውሮ በአሰልጣኝነትና በኬሮግራፈርነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከተወዛዋዠነት፣ አሰልጣኝነት፣ አዘጋጅነትና አማካሪነት ባሻገር በድምጻዊነትና በቴአትርና ፊልም ተዋናይነትም በመሳተፍ ሁለገብ ከያኒነቱን ያስመሰከረ ድንቅ ጥበበኛ ነበር፡፡ በርካታ የሙዚቃ ቪዲዮ ስራዎች ላይ የኪዳኔ ደማቅ የፈጠራና የጥበብ አሻራ ያረፈባቸው ውዝዋዜዎችና ዝግጅቶች ዛሬም፣ ነገም ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡
አሰልጣኝና ኬሮግራፍር እንዲሁም የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በሞያው በሰራባቸው አመታት በርካታ
1. ባለሙያዎች ወደ ሙያው እንዲገቡና የሙያው ስነምግባር እንዲኖራቸው አደርጓል፡፡
2. የባህል ውዝዋዜ ትምህርት ቤት በሌለበት ዘመን በቴአትር ቤቶችና ከቴአትር ቤቶች ውጪ የነበሩ ወጣቶችን አሰልጥናል፤
3. ከከተማ ውጪ በመሄድ ቱባ ባህሎችን በማጥናትና በማምጣት የተለያዩ የባህል ጭፈራዎችንና አለባበሶችን አስተዋውቋል፡፡
4. የውዝዋዜ ሙያ እንደሙያ እንዲታይና አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የተለያዩ መድረኮች ላይ እና ጥናቶች ላይ በመሳተፍ አስተዋኦ አበርክቷል፡፡
5. በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጁ በርካታ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫሎች ላይ በመጋበዝ በዳኝነትና በአማካሪነት ሰርቷል፡፡
6. ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ወጣቶችን ከማሰልጠን አልፎ በደቡብ ክልል ውስጥ የባህል ባንድ ለማቋቋም በቅቷል፡፡
7. በከተማችንና በተለያዩ ከተሞች በተከበሩ የብሄሔር ብሄረሰቦች ክብረ በዓላት ላይ የጥበብ ስራዎችን አቅርባል፡፡
8. በተለያዩ ጊዜ የተከበሩ የአደባበይ በአላት አድዋና የካቲት12 የመሳሰሉት ላይ ስራዋችን አቅርባል፡፡
9. በታላቁ ህዳሴ ግድብ ድረስ በመሄድና ታስቦ በሚከበርበት ጊዜም ስራዎችን አቅርቧል፡፡
10. በመንግስት መስረታና በበአለ ሲመቱ ዝግጅት ላይ ታላቅ የውዝዋዜ ትርኢት በኬሮግራፈርነት ሰርቷል፡፡
11. ሀገራችን የጦርነትና የተፈጥሮ ችግር በገጠማት ጊዜ ከኪነ ጥበብ ስራው ጋር ቀዳሚ በመሆን በርካታ አነቃቂ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
12. የተለያዩ የሀገር መሪዎች፣ አንባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ሲመጡና ሲሸኙ በአየር መንገድና በከንቲባ ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ ደማቅ አቀባበል በማደረግ እና ትርኢቶችን በማቅረብ ባህላችንን አስተዋውቋል፡፡
13. በከተማ ደረጃ የሚዘጋጁ ትላልቅ ሴሚናሮች፤ጉባኤዋችና ሲንፖዚየሞች ላይ የተለያዩ የኬሮግራፈር ስራዎችን ሰርቷል፡፡
ሁለገቡ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ላበረከታቸው ኪነጥበባዊ ስራዎች የምስጋናና የእውቅና የምስክር ወረቀቶችን፡-
Ø ከኢፌድሪ ፊዴሬሽን ምክር ቤት
Ø ከኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር
Ø አዲስ አበባ ዩንቪርስቲ
Ø ከአዲስ አበባ ባህል ኪነ የጥበብና ቱሪዝም ቢሮ
Ø ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት
Ø ከሀገር ፍቅር፤ከቴአትርና ባህል አደራሽ፤ከራስ ቴአትር፤ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአተር እና ሌሎችም በርካታ ተቋማት በክብር ተቀብሏል፡፡
አሰልጣኝ፣ ኬሮግራፍርና የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ሙያው እንዲያድግና ባለሙያውም እንዲጠቀም በነበረው ፍላጎትና ቁጭት ምክንያት ሙያው በተለያዩ ትልልቅ ሆቴሎችና የባህል ምሽቶች እንዲሰራና ባህላችን የበለጠ እንዲተዋወቅ በማማከርና በመደገፍ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
አርቲስት ኪዳኔ ከበርካታ የሀገራችን ታዋቂና ተወዳጅ ሙዚቀኞች ጋር ትላልቅ መድረኮችና በከተማ ደረጃ በቀረቡ ታላላቅ ህዝባዊ በአላትና የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይ የኪሮግራፈር ስራዋችን
Ø በሸራተን አዲስ ሆቴል
Ø በሚሊንየም አዳራሽ
Ø በኢግዚብሽን ማዕከል
Ø በመስቀል አደባባይ
Ø በአዲስ አበባ ስቴድየም
Ø በጊዮን ሆቴል
Ø በሂልተን ሆቴል
Ø በስካይላት ሆቴል በመገኘት ጥበባዊ ስራዎችን ያቀረበ ሲሆን ትልልቅ የቀጥታ የቴሌብዥን ስርጭ የነበራቸውን ግዙፍ መድረኮችም ላይ ልዩ የኬሮግራፈርነት ሙያውን ድንቅ ብቃት አስመስክሯል፡፡
አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በተለያዩ ቴአትርና ሙዚቃዊ ቴአትሮች ላይ በትወናና በዝግጅት ሰርቷል፡፡ በትወና የተሳተፈባቸው ስራዎች፦
Ø ጤና ያጣ ፍቅር
Ø ሮሚዮና ጁሌት
Ø የቀለጠው መንድር
Ø ሊስትሮ ኦፔራ
Ø ከልሺን አውልቂ
Ø ፎርፌ
Ø ኦቴሎ
Ø ቴዎድሮስ
በሙዚቃዊ ድራማ ኬሮግራፈር ዝግጅት፡-
Ø ፎርፌ
Ø ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ነው
Ø ከልሽን አውልቂ
Ø ሊስትሮ ኦፔራ
Ø ሉሲ
Ø ሀገር ማለት ሰው ነው እና ሌሎችም የጠቀሳሉ፡፡
በፊልም ትወና፡-
Ø በህይወት ዙሪያ
Ø ሔሮሽማ
አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከመድረክ ስራዎቹ በተጨማሪም በተላያዩ ታዋቂና አንጋፍ እንዲሁም ወጣት ድምጻውያን የሙዚቃ ቪዲዮ ስራዎች ላይ በኬሮግራፈርነትና በአማካሪነት ሰርቷል፡፡
Ø ለክብር ዳ/ር ጥላሁን ገሠሠ
Ø ለድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ የሰራቸው ስራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
አርቲስት ኪዳኔ በተለያዩ የቴሌቪዥን ዝግጅቶችና የበዓል ፕሮግራሞች ላይ ባቀረባቸው የጥበብ ስራዎች ውበትና ድምቀት የነበረ ሲሆን በፋና ቴሌቭዥን ፋና ሰማንያ የውዝዋዜና ዳንስ ተሰጥኦ ውድድር ላይ በአማካሪነት በመስራት ሙያዊ አስተዋፅዎ አድርጓል፡፡
ሁለገቡ አርቲስት ኪዳኔ በሙያው አድማስ ተሸግሮ በዱባይ እና በታይላንድ ኢትዮጰያንና ባህሏን ያስተዋወቀ ብርቱ የጥበብ ሰው ሰሆን በቅርብ በሀገራችን እና በአለም ህዝቦች ዘንድ አንድ ጊዜ ተሰርቶ ያልተደገመውን የህዝብ ለህዝብ ተጓዥ የሙዚቃ የባህል ቡድንን የሚያስታውስ የሀገረሰብ ሙዚቃዎችን፣ ጭፈራዎችንና ባህላችንን የሚያስተዋውቅ ሉሲ ድንቅነሽ ኢትዮጵያ በሚል በመላው ሀገር ተዟዙሮ የቀረበውን ትርኢት ከባህል ሚንስቴር ኃላፊነት ተሰጥቶት በዋና አዘጋጅነት የውዝዋዜውን ዝግጅት መምራት የቻለ ድንቅ ጥበበኛ ነበር፡፡
ሁለገቡ ከያኒ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት ግንቦት 23/2018 ዓ.ም ድረስ በአንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተዛውሮ በሙያው ወገኑን፣ ሀገሩንና ሙያውን በጥበብ፣ በታማኝነትና በትጋት ሲያገለግል የኖረ፣ በጥበብ ስራዎቹ ስሙን ከመቃብር በላይ ማኖር የቻለ ታላቅ ጥበበኛ ነበር፡፡
አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናዉ የጋብቻ ህይወቱን ከረዥም ጊዜ ፍቅረኛዉ ከወ/ት አይናለም ተፈራ ጋር የካቲት 2 /2018 በክብር ፈፅሟል። ይሁንና ይህ ታላቅ ጥበበኛ ባጋጠመው የጤና እክል ሳቢያ በአዲስ ህይወት አጠቃላይ ሆስፒታል እና በሆፕ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ግንቦት 23/2018 ዓ.ም በተወለደ በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል፡፡
የአርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው የሽኝትና የጧፍ ማብራት ፕሮግራም ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ፣ የሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ለረዥም ዓመታት በሙያው ባገለገለበት አንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግንቦት 25/ 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ በ3፡00 ሰዓት ላይ ከተከናወነ በኋላ የቀብር ሰነ ስርዓቱ በአማኑኤል ካቴድራል ቤተክርስቲያን ይፈፀማል።
የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በመላው ሰራተኞቹና የሙያ አጋሮቹ ስም በሁለገቡ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ፈጣሪ ነፍሱን በመዓዛ ገነት እንዲያሳርፍ ይመኛል፡፡ እንዲሁም ለውድ ቤተሰቦቹ፣ ለዘመዶቹ፣ ለጓደኞቹ፣ ለስራ ባልደረቦቹ፣ ለሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በሙሉ ፈጣሪ ልባዊ መጽናናትን እንዲሰጣቸው ይመኛል፡፡
የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት-ኮምኒኬሽን
#ኪዳኔምስጋናው #ሀገርፍቅርቴአትር #የጥበብሰው #ሀዘን #ኪነጥበብ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen








No comments yet.