ሲዳማ ቡና ወደ ታላቅ ታሪካዊ ምዕራፍ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የአሁኑ ሲዳማ ቡና የቀድሞው ዳራ ከነማ በ1999 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ድንቅ ብቃት በማሳየት እና በኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና 3ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ብሔራዊ ሊግ ያለፈ ክለብ ነው።

ክለቡ ብቸኛ የሲዳማ ዞን ተወካይ ሆኖ በብሔራዊ ሊግ ማደጉን ተከትሎ ፣ የዞኑን ህዝብ እንዲወክል በሚል ስሙ ወደ “ሲዳማ ቡና” ተቀየረ። ይህም ክለቡ ሰፊ የደጋፊ መሰረት እና የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድቶታል።

ሲዳማ ቡና (ዳራ ከነማ) በወቅቱ መቀመጫውንና የመጫወቻ ሜዳውን ይርጋዓለም ከተማ በማድረግ በደማቅ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ከብሔራዊ ሊግ ተነስቶ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመግባት ስኬት ክለቡ በኢትዮዽያ እግር ኳስ ውስጥ በፈጣን እድገቱ እንዲታወቅ አድርጎታል።

ከ 2000 ዓ/ም – 2010 ዓ/ም በይርጋዓለም ከተማ የቆየ ሲሆን በዚህ ወቅት በተለይም በሜዳው ለሁለም የፕሪምየር ሉጉ ክለቦች እጅግ ፈታኝ እንደነበር ይታወሳል። በ 2011 ዓ/ም መቀመጫውንና የመጫወቻ ሜዳውን ወደ ሀዋሳ ከተማ ያዘዋወረ ሲሆን በዚህ አመት በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን ይኸውን ሊጉን በታላቅ ፉክክር በ2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

ክለቡ በ 2017 ዓ/ምበ ኢትዮዽያ ዋንጫ ወላይታ ዲቻን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፎ በክለቡ ታሪክ ትልቁን ስኬት ቢያስመዘግብ በተጫዋች ተገቢነት በሚል ዋንጫው ከወራቶች ቆይታ በኋላ ፌደሬሽኑ በወሰነው ውሳኔ ለወላይታ ዲቻ መሰጠቱ ይታወሳል። ይህም ለክለቡ ቤተሰብ ትልቅ የልብ ስብራት ቢሆንም ክለቡን ወደ ቁጭት እና እልህ ለቀጣይ ድል እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።

በአሁን ሰዓትም አምና ያጣውን የኢትዮዽያ ዋንጫ ከ ወልዋሎ አዲግራት ጋር ለፍጻሜ ያለፈ ሲሆን ፣ ሊጠናቀቅ 4 ጨዋታ ብቻ በቀረው ፕሪምየር ሊግ ከተከታዩ መቻል በ 8 ነጥብ ከፍ ብሎ ከዋንጫው በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ያሉት ሲዳማ ቡና እግርኳስ ክለብ የደጋፊውን የዋንጫ ጥማት ለማርካት የክለቡ የቦርድ አመራር ፣ የደጋፊዎች ማህበር እና ዝናብ እና ፀሀይ ሳይበግራቸው ከጭሪ ፣ በንሳ ፣ አርቤጎና ፣ አሮሬሳ ፣ ሀገረ ሰላም ፣ አለታ ወንዶ ፣ አለታ ጭኮ ፣ ይርጋለም ፣ ሸበዲኖ ፣ ይርባ ፣ በሌላ ፣ ወንዶ ገነት ፣ ውጂግራ ፣ መልጋ ፣ ሀዋሳ እና ከመላው ሲዳማ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎቹ ክለቡ በሚጫወትበት ሜዳ ሁሉ አዳር ተጉዘው በሜዳ በመገኘት በተለያዩ ህብረ ዜማዎች ክለባቸውን 90 ደቂቃ ሙሉ ሲያበረታቱና 12ኛ ተጫዋች በመሆን ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

“ሮሪ ሮሪ ሲዳማ” (Rori Rori sidama) ደጋፊዎች በሜዳ ከሚያሰሟቸው የድጋፍ ዜማዎች አንዱና ሁሌም የሚደመጠው ነው። ትርጓሜውም “ብለጥ ፣ ግነን፣ ንገስ፣ ከፍ በል ፣ በልጠህ ታይ ሲዳማ” እንደማለት ሲሆን ይህም ተጫዋቾች እንዲነሳሱ ትልቅ አቅም ሲሆናቸው ይስተዋላል። ደጋፊዎቹ በዚህ አያበቁም ክለቡ ጎል በናፈቀበት ወቅት በዜማ ወደ ፈጣሪያቸው እንዲህ ሱሉ በዜማ ይማጸናሉ
“ ሂንጎሞና ሂጊንኬ ፣ ማጋኖ አራራሚንኬ
ተኔ ቴኤ ዲአንፎሞና ቴቾላ ፋሪሲኖሞና”
(Hingomona Higinke magano araraminke Tene te’e dianfomona techola farsinomona ) ትርጓሜውም “ተመልሰናል ተመለስልን ፣ እግዚአብሔር ታረቀን ፣ ያንን ይሄን አናውቅም ፣ የዛሬን ብቻ እንማጸንሀለን (እንዘምርልሀለን)
እንደማለት ሲሆን በቅርቡ በኢትዮዽያ ዋንጫ ከመድን ጋር ክለቡ 2-1 እየተመራ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጨተማሪ ደቂቃ ውስጥ ይህ ዜማ እየተዜመ ክለቡ ፍጹም ቅጣት አግኝቶ ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ በመለያ ምት ጨዋታውን ሲዳማ ቡና ማሸነፍ ችሏል። ይህም በተደጋጋሚ ፈጣሪ አድርጎ ስላሳያቸው በሜዳው ከማይቀሩ ዜማዎች አንዱ ነው።

ክለቡ በአሁን ሰዓት ሁለት የሀገሪቱን ትልቅ ዋንጫዎችን በማንሳት አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ከጫፍ የደረሰ ሲሆን ይህን ድል ካሳካ በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያ ትልቁ ድል ሲሆን በክልል ክለቦች ታሪክም ብቸኛው ይሆናል።

በሀገራችን ይህን ድርብ ድል ያሳኩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መቻል እና ኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ ሲሆኑ ሲዳማ ቡና ይህን ድል ካሳካ በሀገሪቱ አራተኛው ክለብ ሲሆን ክለቡም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮዽያን በመወከል በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ ይሆናል።

በዚህ አመት ክለቡ እያሳየ ላለው ታላቅ ጉዞ ከክለቡ ጀርባ ትልቅ የአመራር ብቃትና ብልሀት የታየበት የክለቡ የቦርድ አመራር የአንበሳውን ድርሻ ሲወስድ የደጋፊዎች ማህበር ፣ ተጫዋቾች እና ኮቺንግ ስታፍ ሁሌ ከሜዳ የማይጠፋው ታማኝ ደጋፊዎች ትልቅ ክብር የሚገባቸው ሲሆን ለአመታት የጠበቁትንም ድል በደማቅ ቀለም ለመጻፍ ተቃርበዋል።

Melaku mele yirgalem ✍️
(መላኩ ይርጋዓለም)






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1