ከ14 ሺህ ዓመታት በፊት አምስት ሰዎች ከአንድ የውሻ ዝርያ ጋር የፓይን ዛፍ ቅርንጫፎችን በማብራት ወደ ጣሊያን ዋሻ መግባታቸውን ተመራማሪዎች ገለጹ
#Ethiopia | በሰሜን ምዕራብ ጣሊያን በሚገኘው የባሱራ ዋሻ ላይ የተደረገ አዲስ ጥናት ከ14 ሺህ 400 ዓመታት በፊት በነበረው የድንጋይ ዘመን ማክተሚያ ላይ የነበሩ ሰዎች በጥልቀት ወደ ውስጥ በሚዘልቁ የመሬት ውስጥ መተላለፊያዎች ውስጥ እንዴት ይጓዙ እንደነበር አዳዲስ ማስረጃዎችን ይፋ አድርጓል።
ተመራማሪዎች በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ዋሻውን ለማብራት የተጠቀሙበትን ዘዴ ለማወቅ የአበባ ብናኝ ጥናቶችን፣ የከሰል ፍርፋሪ ትንተናዎችን፣ የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎችን እና የተግባር ሙከራዎችን አቀናጅተው ሰርተዋል።
በእነዚህ ጥናቶች አማካኝነት በወቅቱ በዋሻው ውስጥ የእግር አሻራቸውን ጥለው ባለፉ አምስት ሰዎች ላይ ያተኮረ የመልሶ ግንባታ ስራ ተከናውኗል።
በትዊራኖ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የባሱራ ዋሻ በጣሊያን ካሉ እጅግ ጠቃሚ የቅድመ ታሪክ ዋሻዎች አንዱ ነው። ይህ ዋሻ የሰው ልጆች የእግር አሻራዎችን፣ አብሯቸው የነበረ የውሻ ዝርያ ያላቸውን እንስሳት አሻራ፣ በግድግዳዎች ላይ ያሉ የከሰል ምልክቶችን እና የጥንታዊ ዋሻ ድቦች ቅሪቶችን በውስጡ ይዟል።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች እነዚህን አሻራዎች የኒያንደርታል ሰዎች እንደሆኑ አድርገው አስበውት የነበረ ቢሆንም የራዲዮካርቦን የዕድሜ መለኪያ ፍተሻ ግን ጉብኝቱ የበረዶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ እንደነበር አረጋግጧል።
በ2016 ዓመተ ምህረት የተጀመረው አዲሱ ፕሮጀክት እነዚህ የጥንት ሰዎች እስከ 800 ሜትር በሚረዝመው የዋሻ መዋቅር ውስጥ እንዴት ይንቀሳቀሱ እንደነበር ለመረዳት ያለመ ነበር።
ምስጢራዊው አዳራሽ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በተደረገ ቁፋሮ የተገኙ የከሰል ቅሪቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አብዛኛዎቹ የከሰል ስብርባሪዎች ከፓይን ዛፍ ትናንሽ ቅርንጫፎች የተገኙ ናቸው።
ይህ አዲስ ግኝት ቀደም ሲል የነበሩ ተመራማሪዎች ሰዎች በትላልቅ ዱላዎች የተሰሩ ችቦዎችን ይይዙ ነበር በማለት ያቀረቡትን ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል።
ይልቁንም ሰዎች ከዛፍ ላይ የቆረጧቸውን ትናንሽ የፓይን ቅርንጫፎችን እንደ ተንቀሳቃሽ መብራት ይጠቀሙ እንደነበር ያሳያል።
ይህን ሃሳብ በተግባር ለመፈተሽ ተመራማሪዎች ተመሳሳይ የአየር ንብረት ባለው ሌላ ዋሻ ውስጥ ሙከራ አድርገዋል። በሙከራው መሰረት ሁለት የሚቃጠሉ የፓይን ቅርንጫፎች ለአምስት ሰዎች ቡድን በቂ ብርሃን መስጠት እንደሚችሉና የሰዎች አይን ከጨለማው ጋር ሲላመድ እስከ አስር ሜትር ርቀት ድረስ በግልጽ ማየት እንደሚያስችል ታይቷል።
እነዚህ ትናንሽ ቅርንጫፎች አነስተኛ ጭስ የሚፈጥሩ ከመሆናቸውም በላይ ቡድኑ በጠባብ መተላለፊያዎች ውስጥ በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ ረድተዋል።
ጥናቱ የጥንት የሰው ልጆች በአካባቢያቸው የሚገኙትን የተፈጥሮ ሀብቶች በጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የነበራቸውን ከፍተኛ ብልሃት የሚያሳይ ነው።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#archaeology #italy #prehistory #science #history #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa
Source: GetuTemesgen









No comments yet.