#Ethiopia | በሀገራችን በየዓመቱ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ ሕጻናት በካንሰር በሽታ ቢያዙም አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት የሚችሉት ከ2 ሺህ የማይበልጡት ብቻ ናቸው።
የቀሩት ሕጻናት ደግሞ ስለ በሽታው በቂ ግንባቤ ባለመኖሩ፣ በቅርበት የሕክምና ተደራሽነት በማጣታቸው፣ የባለሙያ እጥረት በመኖሩ እንዲሁም በዝቅተኛ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ በመገኘታቸው ምክንያት ተገቢውን ዕርዳታ ሳያገኙ ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ።
ይህን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የሕጻናት የደምና የካንሰር ሐኪሞች በመተባበር የኢትዮጵያ የሕጻናት የደምና የካንሰር ማኅበርን ተመስርቷል።
ማኅበሩ በበሽታው ለሚሰቃዩ ሕጻናት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለመንደፍ፣ ባለድርሻ አካላትን በጋራ ለማንቀሳቀስ፣ ማኅበረሰቡን ለማንቃት እና የስነ-ልቦና እንዲሁም የማኅበራዊ ድጋፍ ለመስጠት ያለመ ነው።
በተጨማሪም የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት እና በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ ትስስር በመፍጠር፣ በካንሰር ምክንያት የአንድም ሕጻን ሕይወት የማይቀጠፍባትን ሀገር ለመገንባት በቁርጠኝነት ሥራውን ጀምሯል።
ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ማኅበረሰቡን በማንቃት ረገድ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ማኅበሩ ይፋዊ የምስረታ ሥነ ስርዓቱን በሒልተን ሆቴል አካሂዷል።
በዝግጅቱ ላይ ክብርት ሚኒስትሮች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ከፍተኛ ምሁራን፣ ሕጻናትና ወላጆች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም የድርጅት ሥራ አስኪያጆች ታድመዋል።
በተያያዘ ዜና በጨቅላ ሕጻናት ሰብ-ስፔሻሊስት ሐኪሞች የተመሰረተው የኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ማኅበር ይፋዊ የምስረታ ጉባኤውን በዚሁ ዕለት በሒልተን አዲስ አበባ ሆቴል በደመቀ ሁኔታ አካሂዷል።
ይህ ታሪካዊ የምስረታ በዓል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፣ የማኅበሩ አመራሮች፣ የጨቅላ ሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ ባለድርሻ አካላት እና ደጋፊ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተገኙበት በይፋ ተከብሯል።
ይህ ማኅበር ከሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ከጨቅላ ሕጻናት ፌሎው ስፔሻሊስት ተማሪ ሐኪሞች፣ ከጨቅላ ሕጻናት ነርሶች፣ እንዲሁም ማንኛውም በጨቅላ ሕጻናት ጤና ላይ ከሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በሀገሪቱ የሚወለዱ ጨቅላ ሕጻናትን ሕይወት ለመታደግ በትጋት እንደሚሰራ አስታውቋል።
የዚህ ታላቅ የምስረታ ጉባኤ መሪ ቃል ጤናማ ጅምር ለሁሉም አራስ ልጆች የሚል ነበር።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበች ቢሆንም፣ የጨቅላ ሕጻናት ማለትም ከተወለዱ ጀምሮ እስከ 28 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ያሉ ሕጻናት ሞት አሁንም ከፍተኛ ሀገራዊ ትኩረት የሚሻ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሀገሪቱ ከሚከሰቱት ከ5 ዓመት በታች ካሉ ሕጻናት ሞት ውስጥ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ድርሻ የጨቅላ ሕጻናት ሞት ነው።
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆረጠሩ ጨቅላ ሕጻናት ሊከላከሏቸው እና ሊታከሙ በሚችሉ ከመወለጃ ቀናቸው ቀድሞ መወለድ፣ መታፈን እና በኢንፌክሽን ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ።
ይህ አሃዝ እንደሚያሳየው የማኅበሩ መመስረት እና የባለሙያዎች ቅንጅት በሀገሪቱ የእንክብካቤ ጥራትን ለማሻሻል እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ማኅበር መመስረት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ለሚያደርገው አገራዊ ጥረት ታላቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የጨቅላ ሕጻናትን የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት ለማሻሻል የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና ይህ ማኅበር በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የሕክምና አሰራሮችን በመዘርጋት እና የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ረገድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት ድምፀ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ ማኅበሩ ጤናማ ጅምር ለሁሉም ጨቅላ ሕጻን በሚል መሪ ቃል የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዋነኛ ዓላማቸው በኢትዮጵያ የሚወለድ እያንዳንዱ ጨቅላ ሕጻን በወቅቱ የሚገኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፍትሀዊ፣ በሳይንሳዊ ማስረጃ የተደገፈ፣ ከፍተኛ ጥራት ያለውና ርህራሄ የተሞላበት የጨቅላ ሕጻናት ሕክምናና እንክብካቤ እንዲያገኝ ማስቻል እንደሆነ አስረድተዋል።
ዛሬ በይፋ ሥራ ሲጀመር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ መቁረጣቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ማኅበር በሀገሪቱ የሕክምና ሥርዓት ውስጥ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት አራት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
እነሱም በጨቅላ ሕጻናት ሕክምና ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አቅም በስልጠና እና በትምህርት ማሳደግ፣ በሳይንሳዊ ማስረጃዎችና ምርምሮች ላይ የተመሰረቱ የሕክምና አሰራሮችን መዘርጋትና ማሻሻል፣ ለጨቅላ ሕጻናት ጤናና ደህንነት ምቹ የሆኑ ሀገራዊ የጤና ፖሊሲዎች እንዲቀረፁና እንዲሻሻሉ ተፅዕኖ መፍጠር እንዲሁም የጨቅላ ሕጻናትን ጤና በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እና ሰፊ የሕብረተሰብና የሙያተኞች ቅስቀሳ ማካሄድ ናቸው።
ማኅበሩ በሀገሪቱ የጨቅላ ሕጻናትን የጤና ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ከመንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን እያስታወሰ፣ ሕብረተሰቡና የጤና ባለሙያዎች ለዚህ ቅዱስ ዓላማ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አቅርቧል።
#ESPHO #ChildhoodCancer#ESN #Neonatology #HealthcareEthiopia #PediatricOncology #CommunityAwareness #NewbornHealth #EthiopianDoctors #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen









No comments yet.