አከራዮች በራሳቸው ፍላጎት የቤት ኪራይ ማጨመር እንደማይችሉ ተገለጠ::

- Advertisement -
Sidebar AD

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የአከራይና ተከራይ ግንኙነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የጀመረውን የዲጂታል ምዝገባ ሂደት በተመለከተ አዲስ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የመኖሪያ ቤቶች መረጃ ወደ ዲጂታል ቋቱ መግባቱ የታወቀ ሲሆን፣ ይህም አሰራር ከዚህ ቀደም ያለምንም ምክንያታዊ መነሻ በቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ይደረግ የነበረውን ያልተገባ ጭማሪ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀር የቢሮው ኃላፊ መቅደስ ወ/ጊዮርጊስ አስታውቀዋል።

በአዲሱ አሰራር መሠረት አከራዮች በራሳቸው ተነሳሽነት ብቻ የኪራይ ዋጋ መጨመር በሕግ ተከልክሏል።

መንግሥት በየዓመቱ የከተማዋን ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ የገበያ ጥናት ካካሄደ በኋላ የገበያ ዕድገት መኖሩ ከተረጋገጠ ብቻ በየዓመቱ ሰኔ 30 በሚወጣ ይፋዊ መግለጫ መሠረት የዋጋ ጭማሪውን በፐርሰንት ይወስናል።

ለአብነት ያህል የአንድ ቤት ኪራይ አንድ ሺህ ብር ቢሆን እና በመንግሥት ውሳኔ መሠረት የሚፈቀደው ጭማሪ አሥር በመቶ ብቻ ከሆነ፣ ዋጋውን ማሳደግ የሚቻለው ወደ አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር ብቻ ሲሆን ከዚህ ውጭ የተጋነነ ዋጋ መጨመር አይፈቀድም።

የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ገደማ መሙላቱን የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ ቀደም ሲል በአካል ቀርበው ይፈጽሙት የነበረውን አሰራር ለማስቀረት የውል ማደስ ሥራውን በኢንተርኔት ለማከናወን ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት አከራይና ተከራይ ዋጋ ሳይጨመርበት ባለው ስምምነት መቀጠል ከፈለጉ ውላቸውን በኦንላይን በቀላሉ ማደስ የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቷል።

ተከራዮች መብታቸውን አውቀው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ያሳሰቡት መቅደስ ወ/ጊዮርጊስ፣ አከራዮች ዋጋ እንዲጨምሩ ስለጠየቋቸው ብቻ ያለምንም ሕጋዊ መነሻ ክፍያ መፈጸም እንደሌለባቸው ገልጸዋል።

የውል ጊዜው በማብቃቱ ምክንያት ብቻ አከራዮች ተከራዩን አስወጥተው ሌላ ሰው ቢያስገቡ እንኳ፣ ዋጋ ጨምረው ማከራየት ስለማይችሉ ተከራዮች የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ይደረግብኛል በሚል ሊሰጉ እንደማይገባ ተነግሯል።

አብዛኞቹ ውሎች ጊዜያቸው የሚያበቃው ከሰኔ 30 በኋላ በመሆኑ፣ በውል ስምምነት ውስጥ እያሉ ዋጋ መጨመር ፈጽሞ የተከለከለ ነው።

በአጠቃላይ በየሁለት ዓመቱ የኪራይ ውልን በተገቢው መንገድ ማደስ ግዴታ ሲሆን፣ አከራዮችም መብትና ግዴታቸውን ለይተው በማወቅ ሕጋዊ አሰራሩን እንዲያከብሩ ጥሪ ቀርቧል።

መንግሥት በአከራይና ተከራይ መካከል ያለውን ዘላቂ ችግር ለመፍታት የጀመረውን የቴክኖሎጂ ማሻሻያ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበትም ቢሮው አስታውቋል።

AMN


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2