📌 በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት እያለፈ ነው
#Ethiopia | የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የመላመድ የሚያሳድሩትን አሳሳቢ ሀገራዊና አለምአቀፋዊ ተፅዕኖ ለመግታት፣ የተጠናከረ የጋራ ግንዛቤና የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አሳሰበ።
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የመድኃኒት ደህንነት ክትትልና የህክምና ሙከራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አስናቀች ዓለሙ እንደገለጹት፣ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ በአሁኑ ወቅት በሰው፣ በእንስሳትና በዕፅዋት ጤና ላይ እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጠንቅ እየደቀነ ይገኛል። የስራ አስፈፃሚዋ ማብራሪያ እንደሚያሳየው፣ መድኃኒቶቹ በተህዋስያን የመላመድ ባህሪ ካሳዩ በሽታዎችን የመከላከልና የማከም አቅማቸው ሙሉ በሙሉ ስለሚዳከም፣ ህክምና የሚወስዱ ታካሚዎች በደማቸው ውስጥ የሚገኘው ተህዋሲያን መድኃኒቱን ተቋቁሞ በነፃነት እንዲራባና ለህልፈተ ህይወት እንዲዳርግ ያደርገዋል።
ይህ ችግር በተለይ የጤና መሠረተ ልማት ውስን በሆነባቸውና የንፁህ ውሃ አቅርቦት እጥረት ባለባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ላይ የችግሩን አሳሳቢነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል። በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች በዚህ ችግር ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፣ አስፈላጊው እርምጃ ካልተወሰደ እ.ኤ.አ በ2050 የሟቾች ቁጥር 10 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችልና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እስከ 10 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።
አቶ አብዮት አስጨናቂ በባለስልጣኑ የመድኃኒት አግባባዊ አጠቃቀምና የመድኃኒት መረጃ ባለሙያ እንደገለጹት ደግሞ፣ ለዚህ አስከፊ የጤና ቀውስ መባባስ ዋና ዋና ምክንያቶች ከመድኃኒት አጠቃቀም ስህተቶች ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ህብረተሰቡ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ያለ ጤና ባለሙያ ትዕዛዝ በራሱ ፍላጎት መግዛትና መውሰድ፣ የታዘዘለትን የሕክምና መርሃ ግብር ሳይጨርስ ማቋረጥ፣ የመጠን መቀነስና መጨመር ማድረጉ እንዲሁም የሰዓት አጠቃቀምን አለማክበሩ ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ እያፋጠነው ይገኛል ብለዋል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ
Source: GetuTemesgen









No comments yet.