ፊፋ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለተከለከሉት ሶማሊያዊ ዳኛ የዓለም ዋንጫውን ሙሉ ክፍያ ሊፈጽም ነው

- Advertisement -
Sidebar AD

​#Ethiopia | የአሜሪካ ባለስልጣናት ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ በመከልከላቸው ምክንያት ከ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ውጭ ለሆኑት ሶማሊያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዑመር አብዱልቃድር አርታን፣ ፊፋ የውድድሩን ሙሉ ክፍያ እንደሚፈጽምላቸው ሮይተርስ ዘገበ።

​ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዜና ወኪሉ እንደገለጹት፤ ዳኛው በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ላይ ምንም ዓይነት ጨዋታ የማይመሩ ቢሆንም፣ ፊፋ ግን በውድድሩ ተሳትፈው ቢሆን ኖሮ ሊያገኙት የሚገባውን ሙሉ ክፍያ ለመክፈል ቃል ገብቷል።

​እ.ኤ.አ. በ2025 የአፍሪካ ምርጥ ዳኛ ተብለው የተመረጡት አርታን፣ በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ ጨዋታ በመምራት የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ዳኛ ለመሆን በዝግጅት ላይ ነበሩ። ይሁን እንጂ አሜሪካ እንደደረሱ በአሜሪካ የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ባለስልጣናት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
​የትራምፕ አስተዳደር አርታን ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉት፣ “የሽብር ድርጅቶች አባል ናቸው ተብለው ከሚጠረጠሩ ግለሰቦች” ጋር አላቸው በተባለ ግንኙነት መሆኑን አስታውቋል።

​በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጠው ፊፋ በበኩሉ፤ የኢሚግሬሽን እና የድንበር ፖሊሲ ውሳኔዎች በቀጥታ በአስተናጋጅ ሀገሪቱ ስልጣን ስር የሚወድቁ በመሆናቸው ከእርሱ የስልጣን እና የቁጥጥር ክልል ውጭ መሆናቸውን አስገንዝቧል።

​አርታን በዓለም ዋንጫው ላይ የመካፈል ታሪካዊ ዕድላቸውን ቢያጡም፣ ወደ ሃገራቸው ሶማሊያ ሲመለሱ ግን ደማቅ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ለዳኛው ያለውን አጋርነትና ድጋፍ ለማሳየትም፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) የ34 ዓመቱን ዳኛ በመጪው ነሐሴ ወር በፓሪስ ሴንት ጀርሜን እና በአስቶን ቪላ መካከል የሚካሄደውን የዩኤፋ ሱፐር ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ እንዲመሩ መሾሙ ታውቋል።

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2