የድምፃዊ ሰማኸኝ በለው ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

- Advertisement -
Sidebar AD

ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው ከአባቱ አቶ በለው ሹምየ እና ከእናቱ ወ/ሮ እናትነሽ ቢልልኝ መስከረም 17 ቀን 1960 ዓ.ም. የአባይ እና የጣና መፍለቂያ በሆነችው ውቧ ባህር ዳር ከተማ ተወለደ። ያደገውም ቀበሌ 03 (አባ ፋሲሎ ትምህርት ቤት አካባቢ) በተባለው ሰፈር ነው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ለድምፅና ለሙዚቃ ልዩ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ የነበረው ሲሆን፣ በማራኪ ድምፁና በደግነቱ ይታወቅ ነበር። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሰርፀ ድንግል፣ በአባ ፋሲሎ እና በጣና ሃይቅ ትምህርት ቤቶች አጠናቋል። ገና በ14 ዓመቱ በባህር ዳር ሕጻናት ኪነት ቡድን ውስጥ በመሳተፍ የረጅም ዘመን የጥበብ ጉዞውን ጀምሯል።

እሱ ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን የግጥም፣ የዜማና የቲያትር ደራሲ፣ እንዲሁም የባህል ሙዚቃን ከዘመናዊ ስልት ጋር በማዋሃድ የኢትዮጵያን አርሶ አደር ህይወት በመድረክ ላይ ከፍ ያደረገ የጥበብ ጀግና ነበር።

የሰማኸኝ የኪነ-ጥበብ ጅማሮ በ1978 ዓ.ም. የጎጃሙን ዝነኛ “ግሼ አባይ” የኪነት ቡድንን ሲቀላቀል ይበልጥ ደመቀ። በግሼ አባይ ከነይሁኔ በላይ እና ሀብቱ ንጋቱ ጋር በመሆን ለአራት አስርት ዓመታት በሕዝብ ልብ ውስጥ የኖረውን “አንቱየዋ” የተሰኘውን አስደናቂ ሙዚቃዊ ድራማ አቅርቧል።

በ1982 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከታንጎ እና ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤቶች ጋር በመሥራት የመጀመሪያ አልበሙን አሳተመ። “ያዢኝ አላበድሁም” የተሰኘው ሥራውም ከፍተኛ ዝናን አጎናጽፎታል። ከሶስና፣ አይቤክስ እና ሸዋ ጌጥ የምሽት ክለቦች ቆይታው በኋላ፣ በ1990 ዓ.ም በካዛንችስ የራሱን የባህል ምሽት ቤት በመክፈት የጥበብ ሥራው ይበልጥ እንዲጎመራ አድርጓል። በትያትሩ ዘርፍም “የባላገር ፍቅር” በተሰኘው ተውኔት ብቃቱን አስመስክሯል።

ሰሜ በኪነ-ጥበብ ጉዞው ካከናወናቸው ትልልቅ ድሎች አንዱ “ባላገር” የሚለውን ቃል ከኋላቀርነት ትርጉም አውጥቶ የኩራት መገለጫ ማድረጉ ነው። መድረክ ላይ ሲወጣ የአርሶ አደር አልባሳትን በመልበስ፣ “ባላገር ነኝ” ብሎ በመዘመር የገጠሩን ማኅበረሰብ ክብር አሳይቷል። ለዚህም ነው “ሰሜ ባላገሩ” ተብሎ የተሰየመው። የትውልድ ከተማውን ያወደሰበት “ውቧ ባህር ዳር (ዲስካው)”፣ የልጅነትንና የበዓላትን ትዝታ የቀሰቀሰበት “ደቦት እንስራ”፣ እንዲሁም በፈጣን ውዝዋዜ የታጀበው “ዘገኛ” የማይረሱ ሥራዎቹ ናቸው። በተጨማሪም “ኧረ ምኑን ሰጠሽ”፣ “ማነሽ ማነሽ” እና “ዝናቡ” የተሰኙት ዘፈኖቹ ተወዳጅነትን አትርፈዋል። መድረክ ላይ በማይጠፋው ደማቅ ፈገግታው እና ያለ ድምፅ ማጉያ (Mic) መድረክን የመቆጣጠር ተፈጥሯዊ ብቃቱ ወደር አልነበረውም።

ሰማኸኝ ለሕግና ለፍትሕ ከፍተኛ ክብር የነበረው ሰው ነው። በ1991 ዓ.ም. በደረሰ የመኪና አደጋ ተጠርጥሮ የ4 ዓመት እስር ሲፈረድበት፣ አሜሪካ በሥራ ላይ ቢሆንም፣ ሥራውን አቋርጦ በመምጣት ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ እጁን ለፖሊስ በመስጠት ለሕግ ተገዥነትን በተግባር አስተምሯል።

“ሦስት ነገር እወዳለሁ፤ ሀገሬን፣ ትዳሬን እና ሥራዬን” የሚለው ሰማኸኝ፣ በ1982 ዓ.ም. ከወ/ሮ ገበያነሽ አባተ ጋር ትዳር መስርቶ 4 ወንድ ልጆችን በማፍራት አሳድጓል። 4 የልጅ ልጆችንም ለማየት ታድሏል።

​በማኅበራዊ ሕይወቱም ለታመመ ደራሽ፣ አረጋውያንን አቃፊ እና ታማኝ ጓደኛ እንደነበር ወዳጆቹ ይመሠክራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውፍረቱን ለመቀነስ የተለያዩ የሕክምና ዘዴዎችን ሲከታተል የቆየው ሰማኸኝ፣ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጠዋት የድካም ስሜት ተሰምቶት በልጆቹ አማካኝነት ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ በድንገት ሕይወቱ አልፏል። ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎም ለጀግናው ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ማስታወሻ የሚሆን ዜማ ለሕዝብ አድርሶ ነበር።
​ስርዓተ ቀብሩ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

Via: ሀገሬ ቴሌቪዥን






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: