ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ከክፉ ነገር ሁሉ ይከልለን፤ምልጃው እና ረድኤቱም አይለየን

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

ሠራዊት ጌታ የልዑል እግዚአብሔር አገልጋይ “ መላዕክት”

ድርሳነ ሩፋኤል ላይ ተጽፎ እደምናገኘው 7 ሊቃነ መላዕክት ሲኖሩ አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ የስሙ ትርጓሜም “እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው” ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ዙፋን ስር ትዕዛዝ በወጣ ግዜ ኪሩቤል ተቀብለው ለሱራፌል ያስተላልፋሉ፤ ሱራፌልም ለሚካኤልና ለገብርኤል ለሩፋኤልም ያደርሳሉ፡፡ ሚካኤል ለፍጥረቱ በጎም ይሁን ክፉ ትዕዛዙን ይፈጽሙ ዘንድ መላዕክትን ያዛቸዋል፤ ኪሩቤልና ሱራፌል መላዕክቱም ሁሉ አቤቱ የእጅህን ስራ አታጥፋ እያሉ ቀንና ከማታ ይለምናሉ። የመላዕክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያቢሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ እግዚአብሔር ይገስፅህ አለው እንጂ የስድብን ቃል አልተናገረውም ሲባል ሰምተናል፡፡ ሊቀ ነብያት ሙሴ እጅግ ታዛዥና የዋህ ስለነበርና ከንዓንን ለማየት ወደ ናባው ተራራ ሲወጣ 2 መላዕክት በአረጋውያን ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ ቢያይ ላግዛቹ ብሎ መቆፈሪያውን ተቀበላቸው፡፡

በመጨረሻ “ሰውየው በአንተ ልክ ነውና እስቲ ገብተህ ለካልን” አሉት፡፡ እሱም በየዋህነቱ ጉድጓዱ ውስጥ ገብቶ እንደተኛ እንደ እንቅልፍ አሸልቦት በዚያው ዐረፈ፤ መላዕክቱም ቀበሩት። እስራኤላዊያን ሙሴን እጅግ ስለሚወዱት የሙሴን መቃብር እንደ ጣዖት እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን መቃብር ሰወረው፤ ነገር ግን ጠላት ዲያቢሎስ ሊያሳያቸው በመነሳቱ ቅዱስ ሚካኤል ተቃወመው፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ሚካኤል ዲያቢሎስን እግዚአብሔር ይገስጽህ ብሎ ከእርሱም ሰወረበት። በሐዋርያው ይሁዳ መልዕክት ቁጥር 8 የሚገኘው ቃል የቅዱስ ሚካኤልን ትዕግስት ያሳያል፡፡ ዳግመኛም አይሁድ ጌታን ሲሰቅሉት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በቁጣ ሰይፉን አወጣ፤ ቅዱስ ሚካኤል ግን በአይሁድ ስራ አዝኖ ፈጣሪን ፍጡራን ሰቀሉት እያለ በአርምሞና በትዕግስት አያቸው ይላል ድርሳኑ።

ቅዱስ ሚካኤል ሰኔ 12 ቀን ዲያቢሎስን አሸንፎ በምትኩ ሊቀ መላዕክት ሆኖ የተሾመበትና አፎምያንም የረዳበት ቀን ስለሆነ በታላቅ ሥርዓት ይከበራል። ህዳር 12 ሕዝበ እስራኤልን በክንፎቹ ጥላ ከበረሃው ፀሐይ ከልሎ ከግብጽ ምድር እየመራና እየጠበቀ ከንዓን ያገባቸው እለት ነው። መላዕክቱ በክንፋቸው የእግዚአብሔር ስም ስለተፃፈበት ህዝቡን ይጠብቃሉ፤ የመላዕክቱን ስም የመጨረሻውን ፊደል ስናይ ኤል ብሎ ይጨርሳል፡፡ ሚካ-ኤል ገብር-ኤል ኡራ-ኤል፡፡ ይህም “ስሜ በሱ ላይ ነውና” እንደሚል የእግዚአብሔር የምህረት ስም ስለሆነና በክንፎቻቸው ስለተፃፉ መላዕክቱ ይጠብቁናል። “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለአንተ ያዛቸዋል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል” ተብሎም በመዝሙር 90÷11 ተጽፋልና አህዛብን ጭምር ያለጊዜያቸው እንዳይሞቱ መላዕክት ይጠብቋቸዋል!!!

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 33÷7 “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል” ይለናል፡፡ በትንቢተ ዳንኤል 10÷13 እና 10÷21 ደግሞ የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር ዳኛዬ ነው የተባለው ነብዩ ቅዱስ ዳንኤልም ስለ ቅቅዱስ ሚካኤል እንዲህ ሲናገር ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፣ በተዘጋ ጉድጓድ ሲያጽናናው ደግሞ “ከሚካኤል በቀር የሚያጽናናኝ የለም” አለ፡፡ በዓለም ፍፃሜም ስለህዝቡ የሚቆመው ሚካኤል ይነሳል። በማለትረ በምዕራፍ 12÷1 ጽፎልናል፡፡ በራዕይ 8÷3 “የቅዱሳኑ ፀሎት ከዕጣኑ ጢስ ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ” ተብሎ እንደተጻፈውም መላዕክት የቅዱሳኑን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርጋሉ፡፡ ገዳማውያን የሚያደርጉት ጸሎትና የሚያቀርቡት መስዋዕት በእርሱ ምልጃ ያርጋልና ገዳማቸውን እየረዳን በዓታቸውን እያጠናን የበረከታቸው ተካፋይ እንሁን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: