እንኳን ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል አደረሳችሁ፤አደረሰን

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት!!!

ሀገሯ ኪልቅያ ነው፡፡ ባለቤቷ አስተራኒቆስ መስፍነ ኪልቅያ ነበረ፡፡ እርሷም ከባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ደገኛ ሴት ናት ቅድስት አፎሚያ፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን ልደቱን፣ በ21 የእመቤታችንንና በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ ነበር፡፡ ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ምጽዋቱንና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እርሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ጠይቃው አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡ ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ እየሰራች በጾም በጸሎት ተወስና ትኖር ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና ደግ መነኩሴ መስሎ አጋንንትን መነኮሳይያት አስመስሎ መጥቶ ከደጅ ሆኖ አስጠራት፡፡

እርሷም “ከቤት ገብታችሁ በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ፊት ጸልዩልኝ” አለቻቸው፡፡ ሰይጣናቱም “እኛማ በነግህ ጸልየናል?” አሏት፡፡ ቀጥሎም ሰይጣን “እንደው አንቺ ግን ይህ ሁሉ ጾም ጸሎት ምን ያደርገልሻል? ሀብትሽን ሰጥተሸ መጨረስሽስ ስለምንድን ነው? በዚያ ላይ አንቺ ስትደክሚ የሚደግፍሽ ስታረጂ የሚጦርሽ ልጅ የለሽም ሁለተኛ ማግባት ኃጢአት መስሎሻልን? እነ አብርሃም እነ ዳዊት ከብዙ ሴቶች ብዙ ልጆች ወልደው የለምን? አሁንም ቤት ሰሪ ጎመን ዘሪ ልጅ ያስፈልግሻልና ባል አግቢ” አላት፡፡ ቅድስት አፎምያም “አባ ቆብህ መልካም ነበር ንግግርህ ግን ክፉ ነው፣ አትጹሚ አትጸልዪ ያልከኝ፣ ጌታ መጽውት አበድር ሰዋ ብሎ የለምን? ሁለተኛ ባል አግቢ ማለትንስ ከምን አገኘኸው? እርግቦች እንኳ ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ከሌላ ወንድ አይቀርቡም፣ ታዲያ ጥንቱን በንጽሕና ሊኖር የተፈጠረ ሰው ሁለተኛ አላገባም ቢል ዕዳ ፍዳ ሊሆንበት ነውን?” ብላ ሞገተችው፡፡

ሰይጣንም ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡ አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ሲሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እርሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደ ጢስ ተኖ ጠፋ፡፡ በሰኔ 12 ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ ቅድስት አፎምያም “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?” አለችው፡፡ “በእኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም” ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡

ከቤቷ ካለው የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ በመቀጠልም ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ሰይጣናዊ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን “ድረስልኝ” እያለች ስትጠራው ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡ ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ ዕረፍቷ በዚህ ቀን መሆኑን ነግራት፡፡ ሀብቷንም ሁሉ ለቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥታ ሰኔ 12 ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡ ገዳመውያንም የዓለም ደስታ ንቀው በመንፈሳዊ ትጋት ጸንተው ይኖራሉ፡፡ እንደ ቅድስት አፎሚያ ጸጋቸው ለሌሎች ይተርፋል፡፡ ገዳማቸውን ስንደግፍ በዓታቸውን ስናጸና የረድኤታቸው ተካፋይ እንሆናለን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1