የሀዘን መግለጫ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ዓለም አቀፍ እውቅናን የነበረቻው እውቁ የሙዚቃ ማናጀር አቶ አዲሱ ገሰሰ ባደረባቸው ህመም በአሜሪካ ሀገር በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ73 ዓመታቸው ሰኔ 09 ቀን 2018 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

በሙዚቃ ኢንዱስትሪው “የነፍስ አባት” (Godfather) በመባል የሚታወቁት አቶ አዲሱ ገሰሰ የህይወት ፔንዱለም ወደ ሙዚቃ ማናጀርነት ከማዞሯ በፊት በዲሲፕሊን አንፆኛል በሚሉት ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በግራንድ ቴክኒሳንነት ለአንድ አመት እንዳገለገሉ የትምህርት እድል በማግኘታቸው ወደ አሜሪካ ሺካጎ በማቅናት ራንቱል ኤርፎርስ ቤዝ እና ቴክሳስ ላክላንድ ኤርፎርስ ቤዝ ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡

በመቀጠልም ሃሮልድ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ በዛን ስያሜው ሉፕ ኮሌጅ በሚባለው ሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ኖርዝ ኢስተርን ኢሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ ይማሩበት በነበረው ኖርዝ ኢስተርን ኢሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር ታሪክ ወር /Black History Month/ ተብሎ በየዓመቱ የካቲት ወር ላይ በተለያየ መዘክር ወንሞቻቸው ዘለቀ ገሰሰ፤ ሙሉጌታ ገሰሰ፤ እና ጓደኞቻቸውን እነ መላኩ ረታ በዳሎል ባንድ ሙዚቃ እንዲያቀርቡ በማስቻል የማናጅመንቱን ስራ በመስራት የሙዚቃ ህይወት ጉዟቸውን ሀ ብለው ጀመሩ፡፡

በዋሺንግተን፤ በሎስ አንጀለስ በአሜሪካ መድር በኢትዮጵያን ለኢትዪጵያን የመጀመሪያውን የሙዚቃ መድረክ በዳሎል ባንድ ውጤታማ ስራ መስራት ችለዋል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ የማርሌን ቤተሰብ ከነሃብት ንብረቱ በሚያስተዳድሩበት ጊዜ ዘመን አይሽሬውን ኤክሶደስ ሌጀንድ አልበም ከአይስ ላንድ ሪከርዲንግ ጋር እነዲሰራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን አቶ አዲሱ ገሰሰ በማርሌ ቤተሰቦች በሚዘጋጀው አለም አቀፍ የሬጌ ሙዚቃ መድረክ ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ድረስ ለተደረጉት የሙዚቃ መድረኮች የሙዚቃ ጉዞ ሃሳቡን ከመጠንሰስ ጀምሮ ከሁለት አስር ዐመታት በላይ ስራውን በማኔጅመንትነት በመምራት እና በማስተዳደር የዘረጉት መንገድ እስካሁን ድረስ በየዓመቱ የሚደረግን ዓለም አቀፍ የሬጌ ሙዚቃ ፌስቲቫል የማይናወፅ የማእዘን ድንጋይ ተክለዋል፡፡

በየሀገሩ እና ሙዚቃ በተደረገበት መድረክ ሁሉ አቶ አዲስ ፕሮግራሙን የሚያስጀምሩት አባታችን ሆይ በሚለው ቡራኬና ፀሎት በመሆኑ ፌስቲቫሉን የተለየ ድባብ መፍጠራቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ ዚጊን ከጃማይካ የነዘለቀን ዳሎል ባንድ ከሺካጎ ወደኒዮርክ በማምጣት ካጣመሩ በኋላ ከሲግማ ስቱዲዮ ጋር፤ እና ከቨርጂኒያ ሪከርድስ ጋር ውል በማድረግ በአሜሪካ ምድር ቁጥር አንድ አልበም የሆነውን ኮንሺየስ ፓርቲ ማኔጅ በማድረግ ዚጊ ማርሌ የሜሪካንን ትልቁን ግራሚ አዋርድ ሽልማት ሲያገኝ፤ የኢትዮጵያ ዳሎል ባንድ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ባንድ የግራሚ ሽልማቱን እንዲወስዱ በማስቻል ታሪክ የማይረሳው ስራ ሰርተው አልፈዋል፡፡

ለሀገራቸው ኢትዮጵያ የተለየ ፍቅር የነበራቸው አቶ አዲሱ ገሰሰ ከወንድማቸው አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ጋር በመሆን የቦብ ማርሊ 60 ዓመት የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ዝግጅት ኢትዮጵያን መዳረሻ በማድረግ አንድ አመት የፈጀ የዘመቻ /ካምፔይን/ በመስራት በ1997 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ የተካሄደውን የሙዚቃ ፌስቲቫል ስኬታማ እንዲሆን በማስቻል መልካም አጋጣሚ በመፍጠር፤ ሀገራችንን በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ፤ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ፤ እና ኢንቨስመንት ለመሳብ በማለም ዓለም አቀፍ የሆኑ ከ50 በላይ ሚዲያዎችን በመጋብዝ ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ በሙዚቃ ማኔጅመንት የሕይወት ጉዟቸው ያካበቱትን እውቀትና ልምድ በመላ ተጠቅመው ተሰጥዎ ያላቸውን ልጆች በመቃኘት ሀገራቸውን በሙዚቃው ኢንደስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳዳሪ ለማድረግ ትልቅ ህልም ነበራቸው፡፡ በዚህም እጅጋየው ሽባባውን /ጂጂ/ ከአጋራቸው ፓልም ሪከርዲንግ ጋር በመሆን ተወዳጅ የሆነ አልበሟን እንድተሰራ ያደረጉ ሲሆን፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ በሚሰራው ሙዚቃም ማኔጅምቱን በመያዝ ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚጠቀስ ነው፡፡

ይሄም ብቻ ሳይሆን ጃኖ ባንድን በመመስረት እና ለፍሬ እንዲበቁ የአቶ አዲስ ገሰሰ ድጋፍ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ተግባር ነበር፡፡ አቶ አዲስ ጃናናይት የተባለ ተሰጥዎ ያላቸውን ሴቶች የያዘም ባንድ መስርተው ለመጓዝ ያደረጉትንም ጥረት የሚወሳ ነው፡፡ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው “የነፍስ አባት” (Godfather) በመባል የሚታወቁ አቶ አዲሱ ገሰሰ ከሀገራችን ውጪ እንደ ዚጊ ማርሌ፤ ስቴፈን ማርሌ፤ ሎሪን ሂል፣ ፊል ኮሊንስ፣ አርዝ ዊንድ ኤንድ ፋየር (Earth, Wind, & Fire) እና ሌሎችንም በርካታ የሙዚቃ ከዋክብትን በማግኘትና በማስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙዎችን የሙዚቃ ስራ መስመር አሲዘዋል።

አቶ አዲሱ ገሰሰ በሙዚቃ ማኔጅመንት ስራቸው ብቻ ሳይሆን በበጎ ስራ ተግባራቸው የተወደደ አርአያነት ያለው ተግባር ፈፅመዋል፡፡ ከነዚህም መሃከል በግል ከደገፏቸው ግለሰቦች በተጨማሪ በሀገራችን በተለያያ ጊዜ የተፈጠሩ ሰብአዊ ችግሮችን ለመድረስ ያደረጉት አስተዋፅኦ የሚጠቀስ ሲሆን በዋናነት ከወንድማቸው ዘለቀ ገሰሰ ጋር በመሆን በተለያዩ ገጠረማ አካባቢዎች 30 ትምህርት ቤቶችን በማሰራት ያደረጉት በጎ ተግባር በታሪክ የሚወሳ አርአያነት ያለው ተግባር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ መደበኛ መኖሪያቸውን ወደ ኢትዮጵያ ካዞሩ በኋላ በሆቴሊንግ ዘርፍ በመሰማራት ላየንስ ዴን ሆቴልን፤ በማእድን ዘርፍ ዩኒቨርሳል ማይኒንግን፤ በግብርና መስክ አድሶጌት ኩባንያን በማቋቋም የራሳቸውን ጡብ ለማስቀመጥ ቀን ከሌት ያለእረፍት ጥረዋል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ በማህበራዊ ህይወታቸው ቀልድ አዋቂ፤ ተጫዋች እና በቀላሉ ከሰዎች ጋር ተግባብተው የመኖር ፀጋ የነበራቸው ሲሆን ከሁሉም ግን ሰው አካባሪ እና ስነ ምግባር ያለው ቀረቤታቸው ተወዳጅ እና በሰው ልብ አይረሴ አድርጓቸዋል፡፡

አቶ አዲሱ ገሰሰ ከወ/ሮ ሶስና ሽፈራው ጋር በነበረው የፀና ትዳር አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ለማፍራት ችለዋል፡፡

የአቶ አዲሱ ገሰሰ የአስክሪን ሽኝትና ስርዓተ ቀብር አፈጻጸም ስንነስርዓት በቅርቡ እናሳውቃለን ፡፡


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: