#Ethiopia| “የህጻናት ቢጫነት” ህጻናት ከተወለዱ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተመልሰው እንዲታከሙ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን በአበበች ጎበና የእናቶች እና ህጻናት ሆስፒታል የህጻናት ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ኤርሚያስ ጌታቸው ገልጸዋል።
ዶክተር ኤርሚያስ ጌታቸው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት፣ ይህ ችግር በጊዜያቸው የተወለዱ ህጻናትን 60 በመቶ እንዲሁም ያለጊዜያቸው የተወለዱ ህጻናትን 80 በመቶ ሊያጠቃ የሚችል በጣም የተለመደ ክስተት ነው።
ይሁን እንጂ ቢጫነቱ መጠኑ ከፍ ካለ ወደ ጭንቅላት ውስጥ በመግባት ከፍተኛ እና ዘላቂ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል።
የቢጫነት መንስኤዎች
የደም ዓይነት አለመጣጣም- የእናትየዋ የደም ዓይነት ኔጌቲቭ (-) ሆኖ የልጁ ፖዘቲቭ (+) ከሆነ፣ እናትየዋ የምታመነጨው አንቲቦዲ ወደ ልጅዋ በመግባት የቀይ ደም ሴሎችን እንዲሰባበሩ ያደርጋል።
ይህም ለከፍተኛ ቢጫነት፣ ለደም ማነስ እና ለህልፈተ ህይወት ሊዳርግ ይችላል።
በመጀመሪያዎቹ ቀናት እናቶች ህጻናትን በአግባቡ ማጥባት ካልቻሉ ህጻኑ ለድርቀት ይጋለጣል።
ቢጫነት ከሰውነት የሚወጣው በሰገራ አማካኝነት ስለሆነ፣ ህጻኑ በደንብ ካልጠባ ቢጫነቱ በሰውነት ውስጥ ተጠራቅሞ በቆዳና በአይን ላይ በጉልህ ይታያል።
የቢጫነት ምልክቶች እና የሚያስከትለው አደጋ
ቢጫነት በአብዛኛው የሚጀምረው ከራስ ሲሆን፣ ቀስ እያለ ወደ ታች እየወረደ ይመጣል፤የቢጫነቱ ቀለም እስከ እግር እና እጅ ድረስ ከደረሰ ህጻኑ ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኑን ያሳያል።
በወቅቱ ካልታከመና ቢጫነቱ ወደ ጭንቅላት ከገባ እንደ የአተነፋፈስ ችግር፣ ማንቀጥቀጥ፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ የመሳሰሉ አስከፊ ችግሮች ያስከትላል፡፡
በረጅም ጊዜም የአእምሮ ዝግመት፣ የመስማት ችግር፣ የእይታ ችግር እና የሰውነት አካል ሽባ መሆን ጉዳቶች እንደሚያስከትል ዶክተር ኤርሚያስ ያስረዳሉ።
ህክምናው
በሆስፒታል ሁለት አይነት የህክምና አማራጮች አሉእንዳሉት የሚናገሩት ዶክተር ኤርሚያስ አንደኛው፣ፎቶ ቴራፒ (የጨረር ህክምና) ቢጫነቱ ጭንቅላት ውስጥ ካልገባ፣ ህጻኑ በጨረር ህክምና ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ በየቀኑ መጠኑ እየተለካ ወደ መደበኛ እስኪመለስ ድረስ ክትትል ይደረግለታል።
ሌላው የደም ቅየራ ወይም በህክምና ስሙ ኤክስቼንጅ ትራንስፊውዥን ሲሆን ቢጫነቱ ጭንቅላት ውስጥ ከገባ፣ በእምብርት በኩል ደም የመቀየር ህክምና ይከናወናል።
ወላጆች ሊያርጉት የሚገባ ወሳኝ ጥንቃቄዎች
ዶክተር ኤርሚያስ እንደገለጹት፣ ህክምናው ቀላል ቢሆንም መዘግየት ግን የከፋ ጉዳት ያስከትላል። ይህም ረጅም ጊዜ የሚቆዩ ጉዳቶች እንደ አእምሮ ዝግመት፣ የመስማት ችግር፣ የእይታ ችግር እና የሰውነት አካል ሽባነት ሊያስከትል ይችላል።
ብዙ እናቶች ጨለማ ክፍል ውስጥ ይታረሳሉ፤ ይህም የልጁን የቆዳ ቀለም በደንብ እንዳያዩ ያደርጋቸዋል። ይህ ስህተት ነው።
እናቶች መታረስ ያለባቸው በብርሃን ቦታ ነው። እንዲሁም “ለልጁ መብራት አደገኛ ነው” የሚል የተሳሳተ እምነት አለ፤ የቤት ውስጥ መብራት ለልጁ ምንም አይነት ጉዳት አያመጣም ስለዚህ ለጨቅላ ሕጻናት የብርሃን አስፈላጊ ነው ።
ህጻን ከተወለደ በኋላ እናትየዋ የልጇን የቆዳ ቀለም በንቃት መከታተል አለባት። ቢጫነት ካየች ወዲያውኑ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ የልጇን ህይወት ከመታደግም በላይ ከላይ የተጠቀሱትን የረጅም ጊዜ ጉዳቶች ይከላከላል ሲሉም አሳስበዋል።
credit : AMN
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.