ለ207 የልብ ሕሙማን ሕጻናት ነጻ የልብ ሕክምና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

❤ በቀጣይ 1 ሺህ የልብ ሕሙማን ሕጻናት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማሳከም ታቅዷል፣
───
በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የመድሃኒት፣ የግብአት አቅርቦትና አስተባባሪነት ከጤና ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የመንግስትና የግል የሕክምና ተቋማት ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ ከ ኤኘሪል 20/ 2026 – ጁን 10/ 2026 በተካኼደው የተሳካ የልብ ሕሙማን ሕጻናት ነጻ ቀዶ ሕክምና ስራ ላይ ለተሳተፉ አካላት ዕውቅናና ሽልማት ተሰጠ።

በኢትዮጵያ የልብ ማህበር ለረጅም ጊዜ ወረፋ ከሚጠባበቁ ታካሚዎች ውስጥ እና በዲቦራ ፋውንዴሽን የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው የልብ ሕሙማን ሕጻናት በ45 ቀናት ውስጥ ሕክምናቸው በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ መቻሉን ትላንት ሰኔ 14/2018 ዓ.ም ማምሻውን በስካላይት ሆቴል በተካኼደው የምሥጋናና የእውቅና መርሐግብር ላይ ይፋ ተደርጓል።

ሕክምናው በትብብር ሊሰጥ የቻለው ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ በጤና ሚኒስቴር እውቅና ከመንግስትና ከግል ሆስፒታሎችና የሕክምና ተቋማት ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ነው።

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢፌድሪ የቀድሞ ፕሬዝደንትና የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የበላይ ጠባቂ የልብ ሕሙማን ሕጻናት በአጭር ጊዜ ነጻ ሕክምና እንዲያገኙ የተደረገውን ርብርብ በማድነቅ በዚህ ስራ የተሳተፉ ወገኖችን በሙሉ አመስግነዋል።

ስራው ቀጣይነት እንዲኖረውም የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ዶ/ር ደረጄ ድጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በበኩላቸው በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ድጋፍ ሰጪነትና አስተባባሪነት የተከናወነው ስራ ለየት ከሚልበት አንዱ የግልና የመንግስት የሕክምና ተቋማት ለአንድ አላማ ተባብረው የተሳካ ስራ በመሥራታቸው ነው ካሉ በኋላ ይኸ መልካም ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመንግስት በኩል ተገቢውን ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

አቶ ብርሃን ተድላ ፤ የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ መስራችና የቦርድ ኘሬዝደንት ለተገኘው ውጤት ለሁሉም ወገኖች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ (Heart to Heart Children’s Aid) በቀጣይ አዲስአበባን ጨምሮ በ10 ክልሎች የሚገኙና በአቅም እጥረት ሕክምና ማግኘት ላልቻሉ 1 ሺህ የልብ ሕሙማን ሕጻናት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነጻ ሕክምና ሊሰጥ ማቀዱን አቶ ብርሃን አስታውቀዋል።

ከመጪው ጳጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ 1 ሺ የልብ ሕሙማን ሕጻናት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነጻ ቀዶ ጥገና ሕክምና የመስጠት ተግባር እንደሚጀምርም ይፋ ሆኗል። ለዚህም ተግባር እስከ 2 ሚልየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግና ለዚህም ስኬት በኢትዮጵያ እና በአሜሪካን ሀገር በቀጣይ ለማካኼድ በታቀደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶ/ር መለስ ገበየሁ የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የመድሃኒትና ግብዐት አቅርቦት እንዲሁም አስተባባሪነት በመንግስትና በግል የጤና ተቋማት የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስራት ታቅዶ የነበረው ለ175 ሕጻናት እንደነበር አስታውሰው ነጻ ሕክምናውን ግን ለ 207 ሕጻናት በመስጠት የላቀ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በእሳቸው ገለጻ መሰረት :-
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 30፣ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል 30፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ 15 ፣ በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል አማካይነት በጅግጅጋ ሆስፒታል ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በድምሩ 132 ፣ የሕጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና መከናወኑን ዶ/ር መለስ ተናግረዋል።

ለዚህም ተግባር የወጣው ወጪ 400 ሺ የአሜሪካን ዶላር ሲኾን በአሜሪካን ሀገር ከበጎ አድራጊዎች የተሰበሰበው 200 ሺ ዶላር ገንዘብ ግማሹን ወጪ ሲሸፍን ቀሪው በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍና ትብብር እንዲሸፈን ተደርጓል።






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: