ሮቤ፣ ባሌ – ሰኔ 15፣ 2018 ዓ.ም.
#Ethiopia | ኢትዮጵያ በ2030 የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሻገር ጠንካራ ተቋማዊ አቅም፣ የሰው ኃይል ብቃት እና የዲጂታል ሥርዓት ግንባታ ላይ ማተኮር እንዳለባት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ገለጹ።
ዶ/ር አብዮት ይህን ያሉት በመዳ ዋላቡ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው 2ኛው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ “The Responsible AI Revolution: Building Ethiopia’s Institutional Edge in Tourism and Hospitality by 2030” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር ነው።
እንደ አማካሪው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ በዲጂታል ሽግግር ጉዞዋ ከዜሮ እየተነሳች አይደለችም። ባለፉት ሰባት ዓመታት በቴሌኮም ሪፎርም፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በዲጂታል መታወቂያ፣ በክፍያ ሥርዓቶችና በመንግሥት አገልግሎቶች ዘርፍ ጉልህ እድገቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በታኅሣሥ 2018 ዓ.ም. የተጀመረው “Digital Ethiopia 2030” የተሰኘው ብሔራዊ ስትራቴጂ ሁሉም ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ እኩል ዕድል እንዲያገኙ እና የዲጂታል አገልግሎቶች በእምነትና በደህንነት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
ዶ/ር አብዮት እንዳሉት፣ የቱሪዝም ዘርፉ ከዲጂታል ለውጥ በፍጥነት ተጠቃሚ ሊሆን ከሚችሉ ዘርፎች አንዱ ሲሆን፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተደገፉ የቱሪዝም መድረኮች፣ የዲጂታል ትኬትና ክፍያ ሥርዓቶች፣ የጎብኚዎች ፍሰት ትንተና እና የተቀናጀ የቱሪዝም መረጃ ሥርዓት ለዘርፉ አዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
በንግግራቸው የ“MESOB” የተባለውን የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት መድረክ በአርአያነት ያነሱት አማካሪው፣ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንደ አንድ የጉዞ ልምድ እንጂ እንደ ተለያዩ ተቋማት እንደማያዩ ገልጸው፣ የቱሪዝም መረጃ፣ የሆቴል አገልግሎቶች፣ የመጓጓዣ አማራጮች፣ የክፍያ ሥርዓቶችና የደህንነት መረጃዎች በአንድ የተቀናጀ ሥርዓት መሰጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ለዚህም የቴክኖሎጂ፣ የሂደት እና የሰው ኃይል ሦስት ዋና ምሰሶዎች በአንድነት መሠራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ብሮድባንድ ግንኙነት፣ ዲጂታል መድረኮች፣ የመረጃ አስተዳደር፣ የAI ሥነ-ምግባር መመሪያዎች እና የሰው ኃይል ብቃት በጋራ ሲጠናከሩ ብቻ ዘላቂ ለውጥ እንደሚመጣ አስገንዝበዋል።
አማካሪው ኢትዮጵያ በ“5 Million Ethiopian Coders” መርሃ ግብር ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በኮዲንግ፣ በዳታ ትንተናና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ክህሎቶች ማሠልጠን መቻሏ ለዘርፉ ጠንካራ የሰው ኃይል መሠረት እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር አብዮት ባዩ፣ በ2030 የኢትዮጵያ ስኬት የሚለካው በተጠቀመችባቸው የAI መሣሪያዎች ብዛት ሳይሆን በዩኒቨርሲቲዎች የተሻሻሉ ሥርዓተ ትምህርቶች፣ በተቋማት የመረጃ ጥራት፣ በዲጂታል ብቃት፣ በግላዊነት ጥበቃ እና በሕዝብ እምነት ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኮንፈረንሱ በመዳ ዋላቡ ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ትምህርት ዘርፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚያመጣውን ዕድልና ተግዳሮት መወያየት ቀጥሏል።
#Ethiopia #Bale #Tourism #GetuTemesgen #ጌጡተመስገን #ArtificialIntelligence #DigitalEthiopia2030 #MWU
Source: GetuTemesgen









No comments yet.