የቱሪዝም ልማትን ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጋር በማስተሳሰር ሥራ ተጀመረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ሮቤ፣ ባሌ – የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ከ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂ ጋር በማስተሳሰር ወደ ተግባር መግባቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ “የቱሪዝምና መስተንግዶ ትምህርትን በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ማዕቀፍ መቃኘት” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው 2ኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኮንፈረንስ መክፈቻ ላይ ነው።

ዶ/ር በለጠ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ቴክኖሎጂን እንደ ዋና ግብዓት እየተጠቀመች ሲሆን፣ የቱሪዝም ልማትን ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ሥራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በተለይም የሰው ኃይል ልማትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ በቱሪዝም ዘርፍ የሚያስፈልጉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በባሌና ምሥራቅ ባሌ የሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህቦችን በሳይንሳዊ ጥናት በመደገፍ ለልማትና ለማስተዋወቅ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የድሬ ሼክ ሁሴን መስህብ ስፍራዎች ለዚህ ጥረት ተጠቃሽ ምሳሌዎች መሆናቸውንም አክለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፣ የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ በቱሪስት መዳረሻዎችና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ የሚፈለጉ ብቁ ባለሙያዎችን የማፍራት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በሳይንሳዊ ምርምርና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በመደገፍ ማዘመን እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን ሀገራዊ ጥቅም ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

ኮንፈረንሱ በቱሪዝም ልማት፣ በምርምር እና በቴክኖሎጂ ትስስር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ዘርፉን በዲጂታል አቅም ለማዘመን አዲስ እድሎችን እንደሚፈጥር ተገልጿል።

#ሮቤ፣ ባሌ
#Ethiopia #Bale #Tourism #DigitalEthiopia2030 #AI #MaddaWalabuUniversity #GetuTemesgen #ጌጡተመስገን






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: