የኢትዮጵያ ወወክማ እና ካቦድ ማርኬቲንግ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተስማሙ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I የኢትዮጵያ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) ወቅታዊና አሳሳቢ የሆነውን የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ከካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ጋር የትብብር ስምምነት በዛሬዉ እለት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ በመጪው የክረምት ወቅት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ትርጉም ያለው የክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠና እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወወክማ ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተመለከተው፣ ይህ አዲስ አጋርነት ወጣቶችን በእውቀትና በክህሎት በማብቃት ወደ ሥራ ዓለም ለማስገባት የታለመ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የዚህ የወጣቶች ፕሮግራም ዋና አጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በጋራ ሲያከናውን መቆየቱ ነዉ የተገለፀዉ።

በመግለጫዉ ላይ እንደተገለፀዉ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በወወክማ እና በካቦድ ማርኬቲንግ መካከል የሦስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ (Moሀ) ለመፈራረም ሰፊ ውይይቶች ሲደረጉ የቆዩ ቢሆንም፤ ሁለቱ ድርጅቶች በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ቀድመው የጋራ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው የሁለትዮሽ የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱን በቅድሚያ ሊያከናውኑ እንደቻሉ ተገልጿል።

በሀገራችን በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማራውና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ወወክማ (YMCA) በሀገሪቱ የ75 ዓመታት ረጅም የሥራ ልምድ ያለው አንጋፋ ተቋም ነው።

ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 12 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት የማኅበረሰብ ደህንነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ፍትሃዊ ዓለምን መፍጠር በሚሉ አራት ዋና ዋና የፕሮግራም ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የዓለም እና የአፍሪካ ወወክማዎች አባል የሆነው ይህ ተቋም፣ ወጣቶችን በአካል፣ በመንፈስ እና በአዕምሮ የበለፀጉ አድርጎ ለማፍራት ከመንግሥትና ከግል ዘርፉ ጋር ያለውን ስልታዊ አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2