የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለኢትዮጵያና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ነው።

- Advertisement -
Sidebar AD

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በቅርቡ በነበረው የኢራን ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የኤኮኖሚ ቀውስ ለመታደግ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተወሰኑ የአፍሪቃ ሃገራት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ሊያሳድግ ነው። ድርጅቱ ድጋፉን ከማሳደግ በተጨማሪ ገንዘቡን በፍጥነት ለማቅረብ ማቀዱም ተሰምቷል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጁሊ ኮዛክ እንዳሉት በመርኃ ግብሩ ኢትዮጵያ ፣ጋምቢያ እና ቡርኪና ፋሶ ተጠቃሚ ሲሆኑ በተጨማሪ ማላዊ አዲስ የፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ ከተቋሙ ጋር የተፋጠነ ውይይት እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔም የ25 ሚሊዮን ዶላር የትብብር መርሃግብር አካል የሆነውን 6.1 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ከስምምነት መድረሳቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የአይ ኤም ኤፍ (IMF) የአፍሪካ ዳይሬክተር ዘይን ዘይዳን በዋሽንግተን በሰጡት መግለጫ፥ በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የአፍሪካ ቀጠና “ከባድ ፈተና” ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ምንም እንኳን አሁን የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም በጦርነቱ ምክንያት የተስተጓጎለው የባህረ ሰላጤው ሀገራት የኃይል እና የነዳጅ ምርት ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ ከ6 እስከ 7 ወራት ሊፈጅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የነዳጅ ምርት አቅርቦቱ መቋረጥ በአፍሪካ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የነዳጅ እና የማዳበሪያ ዋጋ ንረትን ያስከተለ መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው አይ ኤም ኤፍ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአደጋ ጊዜ ፕሮግራሞቹን እያሰፋ መሆኑን ገልጿል።

እንደ ድርጅቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ያደረጓቸው የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች አሁን ለተከሰተው የኃይል አቅርቦት መናወጥ የተሻለ የመቋቋም አቅም እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል ። ይሁን እንጂ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ የአፍሪካ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ግን አልሸሸገም።

DW Amharic


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: