የሊቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት የአራት አጎራባች የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ አገዱ

- Advertisement -
Sidebar AD

የምሥራቅ ሊቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት የአራት አጎራባች የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ አገዱ። የባለሥልጣናቱ እርምጃ በምዕራባዊ የሊቢያ የባሕር ወደብ በኩል ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚያልሙ ተሰዳጆችን ቁጥር ለመቀነስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል። በሊቢያ ባለሥልጣናት እገዳ የተጣለባቸው የሱዳን፤ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ዜጎች መሆናቸው ተገልጿል። የሊቢያ የባሕር ወደብ የተሻለ ሕይወትን አልመው ወደ አውሮጳ ለመሰደድ የሚሞክሩ በርካታ የአፍሪቃ ተሰዳጆች የሚያዘወትሩት መሸጋገሪያ መስመር ነው።

ተሰዳጆቹ በሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች አማካኝነት ለጉዞ አስተማማኝ ባልሆኑ ትናንሽ ጀልባዎች ከመጠን በላይ ተጠቅጥቀው የሚሳፈሩ ሲሆን ባሕር ላይ በሚያጋጥመው አደጋ በሺህዎች የሚቆጠሩት ካሰቡበት ሳይደርሱ ሕይወታቸው እንደሚቀጠፍ በየጊዜው ይዘገባል። ትናንት ይፋ የተደረገው እገዳ የሱዳን፤ የኤርትራ፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ተሰዳጆች በየብስም ሆነ በባሕር እና በአየር ወደ ሊቢያ ግዛት እንዳይገቡ ከልክሏል። መግለጫው አክሎም ክልከላው ዲፕሎማቶች፤ የጤና እና የትምህርት ዘርፍ ሠራተኞችን እንደማይመለከት አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ከሌላ ሃገር ወደ ሊቢያ የሚላኩ ስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ በምሥራቅ እና ምዕራብ የሊቢያ መንግሥታት መካከል ላለፉት ወራት ውጥረት አስነስቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ስደተኞች ላይ በተደረገው ክትትል በሺህዎች የሚቆጠሩ በዚሁ ምክንያት ታስረዋል። የተመድ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሊቢያ ውስጥ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የሱዳን ዜጎች ናቸው። አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚፈልጉ ቢሆንም ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች በባሕር ላይ ቃኚዎች እየተያዙ ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ እየተደረገ ነው። ስደተኞቹ በሊቢያ መንግሥታት እስር ቤቶች የሚያዙ ሲሆን እንግልት፤ የግዳጅ የጉልበት ሥራ፤ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈር እና ማሰቃየት እንደሚፈጸምባቸው ተገልጿል። የተመድ መርማሪ ኮሚሽንም ስደተኞቹ ላይ የሚደርሰውን እንግልት በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው ብሎታል።

DW Amharic



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1