#Ethiopia | የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮችና ደረጃዎች ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ 83 እጩ ተማሪዎች ነገ በታላቅ ድምቀት እንደሚያስመርቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ገለጹ።
ዘንድሮ ለምረቃ ከበቁት ተማሪዎች መካከል 2 ሺህ 882ቱ ወንዶች ሲሆኑ፣ 1 ሺህ 201ዱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። እጩ ምሩቃኑ በቆይታቸው በርካታ ፈተናዎችን በስኬት የተወጡና በተለይም ደግሞ በሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ላይ ከፍተኛና አጥጋቢ ውጤት በማስመዝገብ ለዚህ ማዕረግ የበቁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲው እየተገበደደ ባለው የትምህርት ዘመን በመማር-ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡ የተነገረ ሲሆን፣ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው «Center for World University Rankings» የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ባወጣው የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት ተቋሙ ከሀገር ውስጥ 2ኛ እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ 4ኛ ደረጃን መያዙ ነው።
ይህም የጎንደር ዩኒቨርሲቲን በዓለም ላይ ካሉ ከ21 ሺህ በላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምቶቹ 7.8 በመቶ ውስጥ እንዲመደብ ያደረገው ታላቅ የሀገር ስኬት መሆኑ ተብራርቷል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ለስምንት አንጋፋ ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እድገት መስጠቱ የተቋሙን የምርምር አቅም የሚያሳድግና ወደ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት ለሚደረገው ሽግግር ትልቅ ግብዓት የሚሆን ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
የዘንድሮውን የምረቃ ስነ-ስርዓት ለየት ከሚያደርጉት ሁነቶች መካከል ዩኒቨርሲቲው ከአምስት ዓመታት በኋላ በአዲሱ መመሪያ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያበረክተው የክብር ዶክተሬት ሽልማት አንዱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የተቋሙን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ ቃል ከተገቡት ዕቅዶች መካከል በጤናው ዘርፍ ልዩ አበርክቶ ላላቸው አካላት የሚሰጠው ተስፋ ሰጪው አመታዊ የጤና ሽልማት (Health Award) በአራት ዘርፎች ተከፋፍሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ለተሸላሚዎች ይበረከታል።
በተመሳሳይ መልኩ በሙያቸውና በሃላፊነታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት የሚሰጠው አዲሱ ፕሬዝዳንታዊ ሽልማት በነገው እለት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ ያጠናቀቃቸውን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያስመርቅ ያስታወቁት ዶክተር አስራት አጸደወይን፣ ተቋማቸው ወደ ራስ-ገዝነት ለመሸጋገር ሁሉንም ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።
ይህ የምረቃ በዓል ዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ ራሱን ወደ ማስተዳደር ሂደት ከመሸጋገሩ በፊት የሚከናወን የመጨረሻው ታሪካዊ የምረቃ መርሃ ግብር ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ፣ ለተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጌትነት ተመስገን
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ
Source: GetuTemesgen









No comments yet.