መንትዮቹ መንትዮቹን አገቡ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​በናይጄሪያ ደቡብ ምዕራብ ከተማ ኢባዳን የተፈጸመ አንድ ልዩ ሰርግ በታዳሚዎችና በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

ታይዎ እና ኬሂንዴ ኦጉንቶዬ የተባሉ መንትያ ወንድማማቾች ታይዎ እና ኬሂንዴ አደዲራን የተባሉ ተመሳሳይ ስምና መልክ ያላቸውን መንትያ እህትማማቾች በጋራ ሰርግ አግብተዋል። በዮሩባ ባህል መሠረት ለመንትዮች የሚሰጡት ስሞች አስቀድመው የተወሰኑ በመሆናቸው የመጀመሪያው ልጅ “ዓለምን የሚፈትን” ትርጉም ያለው “ታይዎ” ሲባል፣ ሁለተኛው ደግሞ “በኋላ የመጣ” በሚል “ኬሂንዴ” ተብሎ ስለሚጠራ የሙሽሮቹ ስም መመሳሰል ለሠርጉ ታዳሚዎች ልዩ ግርምት ፈጥሮባቸዋል።

​አሁን በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ጥንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ከ10 ዓመታት በፊት በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ በነበረበት ወቅት በአንድ መምህራቸው አማካኝነት ነበር። ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ እህትማማቾቹ ለግንኙነቱ ፈቃደኛ ባይሆኑም ከዓመታት ቆይታና በተለያዩ ሀገራት ካደረጉት ጉዞ በኋላ ግንኙነታቸው እያደገ መጥቶ ለዚህ አስደሳች ቀን በቅተዋል። ወንድማማቾቹ ከመንያ ሚስቶቻቸው እያንዳንዳቸው መንታ ልጆችን የመውለድ ትልቅ ምኞትና ጸሎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

​የሙሽሮቹ ቤተሰቦችና ታዳሚዎች በሁኔታው እጅግ መደሰታቸውን የገለጹ ሲሆን ሙሽራው ኬሂንዴ ኦጉንቶዬም “ሚስቶቻችን በጣም ከመመሳሰላቸው የተነሳ የገዛ ቤተሰቦቻቸው እንኳ አንዳንድ ጊዜ ያቀያይሯቸዋል እኛ ግን የየራሳችንን ሚስት ጠንቅቀን ስለምናውቅ በጭራሽ አንቀያይርባቸውም” ሲል የቡዙሃኑን ስጋት ሞግቷል።

መንትያ ልጆች በጣም በሚከበሩበትና ቁጥራቸውም በከፍተኛ ደረጃ በሚገኝበት በዮሩባ ማኅበረሰብ ውስጥ የተፈጸመው ይህ ጋብቻ፣ በፈጣሪ ፈቃድ የተከናወነ ድንቅ ክስተት ተብሎ ተወድሷል።

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2