ትላልቆቹን ጨምሮ የገንዘብ ተቋማት በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ለመንግስት የሚያበድሩ ከሆነ የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ እጥረት ሊገጥመው እንደሚችል ባለሞያዎች እየተናገሩ ነው።
ለካፒታል የተመደበው በጀት ከቀዳሚው ዓመት ብዙም ዕድገት አለማሳየቱም የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።
የ2019 የፌዴራል መንግስት አጠቃላይ በጀት 2 ነጥብ 34 ትሪሊየን ብር እንዲሆን ረቂቅ ተዘጋጅቷል።
ከዚህ በጀት 1 ነጥብ 8 ትሪሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ በሚሰበሰብ ገቢ እንዲሸፈን መታሰቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ፤ በረቂቁ ዙሪያ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ ተናግረዋል።
ቀሪውን 522 ቢሊየን ብር ደግሞ በዋናነት በመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ ለመሙላት እንደታሰበ ጠቅሰዋል።
ጉድለቱን ለመሙላት ከብሄራዊ ባንክ የሚወሰድ ብድር ግን አይኖርም ተብሏል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ዋስይሁን በላይ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድም የግሉ ዘርፍ በቂ ብድር እንዳያገኝ ሊያደርግ እንደሚችል ይናገራሉ።
በባንኮች የብድር ጣሪያ ላይ ከተቀመጠው ገደብ እና በየጊዜው ከሚካሄደው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ጋር ሲደመር አሰራሩ የግሉ ዘርፍ ብድር የማግኘት ዕድል ጫና አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል ለአመቱ ከተያዘው በጀት 568 ነጥብ 2 ቢሊየን ብሩ ለካፒታል ወጪ የተመደበ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በ2018 ለካፒታል ወጪ ተመድቦ የነበረው 415 ቢሊዮን ብር ነው ። ልዩነቱ ሲታይ ለካፒታል ወጪ የተመደበው ገንዘብ ብዙም ዕድገት አለማሳየቱን መረዳት ይቻላል።
ሁኔታው መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር ላይ ትንሽ ያዝ ማድረግ መፈለጉን ያሳያል የሚሉት አቶ ዋሲሁን ትኩረቱ የነበሩትን መጨረስ ላይ አድርጓል ሲሉም አክለዋል፡፡
መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ቆጠብ ሲል ሊፈጠር የሚችል የስራ ዕድልም አብሮ ይቀንሳል የሚሉት ፤የምጣኔ ሃብት ባለሞያው አቶ ዋሲሁን አማራጩ የግሉ ዘርፍ ማሳተፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ያገኙትን በጀት ለካፒታል ወጪ ማዞር ከቻሉ ግን ገንዘቡ ትንሽ እንዳልሆነ አቶ ዋሲሁን ተናግረዋል።
ዋናው ጉዳይ የተመደበው የካፒታል በጀት ስራ መፍጠር እና የወጪ ንግድን ለሚያሳድጉ ዘርፎች መዋሉ ነው ብለዋል።
ለካፒታል ወጪ ከፍተኛ ገንዘብ ቢመደበም የሚሰበሰበው ገቢ ካላደገ የበጀት ጉድለቱ ከፍ ከማለት ውጪ ሊተገገበር እንደማይችል የምጣኔ ሃብት ባለሞያው አቶ ዋሲሁን ተናግረዋል።
Sheger Fm
Source: Yeneta Tube









No comments yet.