በአንዳንድ ክፍለከተሞች በቤት ኪራይ ዉል ላይ የተቀመጠዉ የዋጋ ተመን እና ቤቱ የማይጣጣም እንደሆነ እየታወቀ እንኳን ጭማሪዉ በ…

- Advertisement -
Sidebar AD
በአንዳንድ ክፍለከተሞች በቤት ኪራይ ዉል ላይ የተቀመጠዉ የዋጋ ተመን እና ቤቱ የማይጣጣም እንደሆነ እየታወቀ እንኳን ጭማሪዉ በዉሉ መሠረት እንዲሆን ተደርጓል ሲል የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ገለፀ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ እንደገለፁት፥ “የ11.5 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የተደረገዉ ዉሉ ላይ በተቀመጠዉ እንጂ በደበቃችሁት ላይ አይደለም “ሲሉ  ከአከራይ ተከራይ ተወካዮች ጋር በተደረገ ዉይይት ላይ ተናግረዋል።
ሰኔ 30 ጀምሮ የሚተገበረዉ የቤት ኪራይ ዋጋን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አመታዊ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መተመኛ ጥናት በትናንትናው ዕለት ለዉይይት ቀርቧል።
ስለጥናቱ ገለፃ ያደረጉት በአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ተመራማሪዉ አቶ ኑርአሁን አንዳርጌ፥በዚህ ጥናት የዋጋ ትመና ለማድረግ የተለያዩ መስፈርቶች መካተታቸውን ገልፀዋል።
የዋጋ ግሽበት፣ የቤቱ መገኛ እና የቤት ስፋት እንዲሁም ከመንገድ ያለ ርቀት ያሉ ከግምት ማስገባቱ ተገልጿል።
ተመራማሪዉ ጥናቱን ለማድረግ በከተማዋ ያለዉን የህዝብ ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበር በመግለጽ የህዝቡ ቁጥር መብዛት የፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን ፈጥሯል ብለዋል።
እስከአሁን ወጥ የሆነ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት 28 በመቶ አከራዮች በየጊዜው በዘፈቀደ የዋጋ ማሻሻያ ያደርጉ እንደነበር በመድረኩ ተገልጿል።
በጥናቱ የተሳተፉት ተመራማሪዉ እንዳስረዱት አከራይ እንደፈለገ ዋጋ ቢጨምር አብዛኛውን ሰዉ በረንዳ ይወጣል ፤ ይህ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የሚያስገድድበት አሰራር ሆኖል ብለዋል።
በአለምአቀፍ ደረጃ አንድ ሰዉ ከገቢዉ ለቤት ኪራይ 30 በመቶ መክፈል ያለበት ቢሆንም በኢትዮጵያ አሁን ላይ በተገኘዉ ጥናት አንድ ሰዉ ከገቢ ላይ የቤት ኪራይ ወጪዉ ከ50 እስከ 80 በመቶ እንደሚደርስ ተጠቁሟል።
በትናንትናው የዉይይት መድረክ የተካፈሉ የአከራይ እና ተከራይ ተወካዮች በዋጋ ጭማሪዉ ዙሪያ ለአስተዳደሩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ከአራዳ ክፍለከተማ እንደመጡ የተናገሩት ተሳታፊ ሀሳባቸውን ሲገልፁ፥”አከራዩም ሆነ ተከራዩ የችግሩ አካል ነዉ፤ በዚህ ላይ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል”ይላሉ።
የ11.5 በመቶ የዋጋ ጭማሪዉ ለአከራዩም ሆነ ለተከራዩ የዋጋ ተመኑ ሚዛናዊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። 
ሌላኛዉ ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ እንደመጡ የገለፁ ተሳታፊ በቤት ኪራይ ዙሪያ በአከራይ እና በተከራይ በኩል የመደባበቅ ሂደቶች አሉ ፤ ይሄንን ግልፅ ማድረግ ካልተቻለ ፍትሀዊ የአከፋፈል ስርአት ማምጣት እንደማይቻል አንስተዋል።
በመድረኩ የ11.5 በመቶ ዋጋ ጭማሪ በመሀል ከተማ እና በማስፋፊያ አካባቢዎች ለምን እኩል ይጨመራል? ይህን ጭማሪ አሁንስ ተከራዩ ጨምሮ መክፈል ይችላል ወይ? የሚሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።
ለተነሱ ሀሳብ እና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቢሮዉ ሀላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ፥ በዉሉ መሠረት የተቀመጠዉን ዋጋ መነሻዉ ተንተርሶ በጥናቱ መሠረት ጭማሪ  መደረጉን ገልፀዋል።
በአንዳንድ ክፍለከተሞች በቤት ኪራይ ዉል ላይ የተቀመጠዉ የዋጋ ተመን እና ቤቱ የማይጣጣም እና የማይገጣጠም እንደሆነ እየታወቀ እንኳን ዉሉ ህጋዊ አድርገን ጭማሪዉ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
የ11.5 በመቶ የዋጋ ጭማሪ የተደረገዉ ዉሉ ላይ በተቀመጠዉ እንጂ በደበቃችሁት ላይ አይደለም በማለትም ገልፀዋል።
“ዋጋ ሲጨመር ዉሉ ላይ ባለዉ ነዉ የተጨመረዉ መጀመሪያ ስታከራዩ በማስፋፊያ እና በመሀል ከተማ በልዩነት እንዳከራያችሁ ሁሉ አሁን የተጠናዉ ጭማሪ በዉሉ መሠረት የሚጨምር ነዉ፤ ለማስፋፊያ አካባቢ ዝቅ ያለ ለመሀል ከተማ ከፍ ያለ ጥናት አልተጠናም “ሲሉ አስረድተዋል።
በመጪዉ አመት 11.5 በመቶ ጭማሪ የተደረገበትን አግባብ ያስረዱት ሀላፊዋ፥”ጭማሪዉ በጣም ከፍ ያለ ነዉ ብለን እኛ አልወሰድንም ቢያንስ የፌዴራል ጥናትን እንኳን ወስደን ተግባራዊ ብናደርግ  እንደ ከተማ አስተዳደር  ጥናት ዉስጥ ስናስገባዉ ትንሽ ነዉ የጋሸበዉ ፤ ይሄን ተከራዩ መክፈል ይችላል ብለን ነዉ  የወሰድነዉ” ሲሉ አስረድተዋል።
በከተማዋ ከ50 ሺህ በላይ የኪራይ ቤቶች ተመዝግበዉ ወደ ሲስተም እንደገቡ ተገልጿል።
@Seledadotio
@Seledadotio

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1